ኢሕአዴግ ይበልጥ እየከፋ ነዉ፣ እኛም ወደ ተሻለ ነገር እያቀናን ነዉ!

በእምነት ጣልቃ መግባትን ከኦርቶዶክስ ቤተእምነት ወደ ሙስሊሙ እምነት ያስፋፋ፤ በዋልድባ የገዳም መሬትን በመንጠቅ - ኢትዮጵያዉያንን ነቅሎ ባዕዳንን ሊያሰፍር የሚሯሯጥ ፤ አሁን ደግሞ የዘረኛዉ ፖሊሲ ሎጂካል ድምዳሜ የሆነዉን የቤንቺ ማጂ ነዋሪ የሆነዉን የአማራዉን ሕዝብ ከአካባቢዉ ‘ማጽዳት’ የያዘዉ የኢሕአዴግ/ሕወሐት አምባገነን መንግሥት፣ የበለጠ እየከፋ መጥቷል። ይህ እኛን አላስገረመንም - ሲፈጸም እጅጉን አሳዘነን እንጂ።

እስከመቼ? ይህን ሰይጣናዊ ሥርዐት እስከመቼ እንደልቡ እንዲፏልል ልንፈቅድለት ይገባል? ምሱስ ምንድን ነዉ?

እዚህ እንዲደርስ፣የመንግስት ስልጣንነ እንዲጨብጥ የፈቀድንለት እኛዉ ስለሆንን፣ የምንነፍገዉም እኛዉ ነን። በእዉነት ኢሕአዴግ/ሕወሐት የወሎ፣የጎንደር፣የጎጃም እና የሸዋ ሕዝብ ሳይፈቅድለት፣ ሳይረዳዉ፣ አዲስ አበባ ገባን?! ሕዝቡ ባንድነት (ከሞላ ጎደል እንበለዉ) በመፍቀዱ አይደል ኢሕአዴግ/ሕዉሐት ድልን የተጎናጸፈዉ?! ይህ፣ ተጋደልቲዉን ለማናናቅ ፈጽሞ አየደለም። ለትግሬ ጦረኝነትና ጀግንነት ምስክርም አያስፈልገዉ - ኢትዮጵያዊ ነዉና! የሩቁን ትተን የቅርቡን የአደዋን ታሪክ ያየ - የኦሮሞ ፈረሰኛ፤ የአማራዉ፣የትግሬዉ፣የጉራጌዉ፣ የአገዉ፣ወዘተረፈ ነፍጠኛ፣ አይበገሬ ኢትኦጵያዊ፣ ያመጣዉ ዉጤት ዛሬም እሰከዘልአለሙም ይዘከራል።

ታዲያ ይህን የመሰለ ታሪክ ካለዉ ሕዝብ መሐል ወጥቶ፣ ተዉ የሚለዉ ጠፍቶ፣ መሐል ያስገባነዉን ኢሕአዴግ/ሕዉሐትን ከሥልጣን ማስወገድ ለትግሬዉም፣ለኦሮሞዉም፣ለአማራዉም፣ለሁሉም አቃተዉ። ለምን ቢባል፣ ምሱን መስጠት አቅቶን።

በአንድ ወቅት አንድ ሁኔታዉን የታዘበ ተቃዋሚ ታጋይ፣ ተቃዋሚዎች ኢሕአዴግ/ሕወሐትን ከየአቅጣጫዉ ‘ከበዉ’ የየአቀማቸዉን እየሰነዘሩበት ነዉ - ነገር ግን የሁሉም የተበታተነ ስንዘራ እንደመጉዳት ፋንታ ኢሕአዴግን ግራ ቀኝ ደግፎ እነደሐዉልት አቆመዉ ያለዉን ያስታዉሰናል። ታዲያ ምሱ ምን ይሆን?

ምሱ አንድነት ነዉ! የኢትዮጵያዊ ተቃዋሚዎች አንድነት!! የኢትዮጵያዊ ተቃዋሚዎች ሁሉ አንድነት!!! ኢትዮጵያዊ ተቃዋሚዎች ሁሉ በአንድነት ተሰልፈዉ በአንድ ጸረ-ኢሕአዴግ/ሕወሐት አቅጣጫ መግፋት ብቻ ነዉ!!!!

የፖለቲካ ናችሁ ወይ የሲቪክ ድርጅት፤የብሔረሰብ ድርጅት ናችሁ ወይስ የሕብረ-ብሔር ፤ሙስሊሞች ናችሁ ክርስቲያኖች፣ሳንል እንደ አንድ ሰዉ መቆም ይኖርብናል። ፍጹም አንድነት ባንዴ ባይገኝም፣ ቢያንስ ከአሁኑ በሚደረጉ የመግባቢያ ስምምነቶች (Memorandum of Understanding) እየተደረጉ በኢትዮጵያዊነታቸዉ የሚያምኑ ሃይሎች ያለምንም ሰበብ ባነድ ላይ መቆም ይችላሉ፣ አለባቸዉም!! ኢሕአዴግ በሕዝቡ ላይ አስከፊ እርምጃ በወሰደ ቁጥር ከንፈርን መምጠጥና መግለጫ ማንጋጋት(ይህ አይቆጠርብንና!) ትርጉም የለዉም።

ይህን በተመለከተ ጥር 2002 ታጠቅ ባወጣዉ ቁ.24 መግለጫ “የአንድነት መዘግየት ለኢሕአዴግ/ሕወሐት የበቀል ሰይፍ ተናጠል ሰለባነት መመቻቸት ነዉ” ብሎ ነበር። ከላይ ለተጠቀሱት ችግሮቻችን ተለያይቶ መጮሁ ከዚህ በፊት ለነበሩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ እንዳላመጣ ሁሉ፣ አሁንም ዘላቂ መፍትሄ ስለማያመጣ፣ በአንድነት፣በአንድ አቅጣጫ፣ ሃይላችንን አስተባብረን ኢሕአዴግ/ሕወሐትን እንግፋዉ እንላለን።

ሰይጣኑ አይስማብንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመሩ የሕብረት፤የጥምረት ሙከራዎች እጅጉን የሚያበረታቱ በመሆናቸዉ የምር ተጠናክረዉ እንዲወጡ፣ ወደሗላ ሳንመለከት፣ በአንድ ላይ ወይም በትብብር እንዲሰሩ ለማድረግ የሁላችንም ጥረት ያስፈልጋል። ታጠቅ የበኩሉን ትብብር በማድረግ ላይ ነዉ። ሳናወላዉል ሁላችንም ለአንድነት የምንሰጠዉ የሃሳብ፤ የማቴሪያልና የመንፈስ ድጋፍ፣ ለኢሕአዴግ/ሕወሐት ምሱ ነዉ። አንድነት አቀበቱን ያወጣናል፣ የቀረዉ ቁልቁለት ነዉ!

በሙስሊሞች መሐል ልዩነትን ማባባስና በእምነት ጣልቃ መግባት ይቁም!

የዋልድባ መሬት ዘረፋ ይቁም! የእምነት ገዳም ይከበር!

የአማራዉን ሕዝብ የማፈናቀልና የማዋከብ እርምጃ አሁኑኑ ይቁም! ሕዝባችን መልሶ እንዲቋቋም እንታገል!

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘልአለም ይኑር!

_______________________________________________________________________________________________________________________________

E-mail: tatekethiopia@hotmail.com www.tatekethiopia.com