ለአንድነትና ለዴሞክራሲ፣ በአንድነት!

በስተሰሞኑ የግንቦት 7 ንቅናቄ ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት አድርጋናለች ከሚሉ ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ መድረክ መስጠቱን በተመለከተ ብዙ ዉይይት እየተካሄደ ይገኛል። በዚህ ጉዳይ ላይ የሚደረገዉ ዉይይት አንዳንዶችን በግንቦት 7 ማንነት ላይ ጭምር ግራ እሰከመጋባት አድርሷል። ልዩነቱ አንዳንዴም የታክቲክ አንዳንዴም የፍልስፍና ወይም የርዕዮተዓለም እየመሰለ፡ ሁኔታዉን በማወሳሰብ እንደተለመደዉ ከኢሕአዴግ ጋር የሚካሄደዉን ትግል ሊያዘናጉ ከሚነሱ ጉዳዮች ተርታ በመግባት ላይ ያለ በመሆኑ፡ በቶሎ መልስ መስጠቱና ልናተኩርበት ወደሚገባዉ ጉዳይ ማለፉ የተሻለ ነው ብለን እናምናለን። ለጉዳዩ አጥጋቢ ትንተና ለመስጠትም፡ ጉዳዩን ከመሰረቱ አንስቶ በየደረጃዉ መመልከት ይሻል።

 1. የአንድነት ሃይሎች እነማን ናቸዉ?

በዛሬይቷ ኢትዮጵያ የአንድነት ሃይሎች ብለን የምንጠራቸዉ፡ በጸረ-ኢሕአዴግነት የተሰለፉ፡ በኢትዮጵያ አገራዊ አንድነት፣ በኢትዮጵያዊነት፣ እና በዴሞክራሲያዊ ሰርዓት ግንባታ የሚያምኑ፡ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ የሲቪክ ማሕበራት፣ ማንኛቸዉም ሕዝባዊ ማሕበራትና ድርጅቶች እና ታዋቂ ግለሰቦች ናቸዉ።

 1. የትግሉ አብይ ዓላማ ምንድነዉ?

የሕወሀት/ኢሕአዴግን አምባገነን አገዛዝ፡ በሕዝባዊ ተቃዉሞ ከሕዝብ ጫንቃ ማስወገድና፡ የሰዉ ልጅ እኩልነት በሁሉም አቅጣጫ የሰፈነባት፣ የሕግ የበላይነት የነገሰባት፣ የሕገመንግስት ዋስትና ያላት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መመስረት።

 1. የትግሉ ደረጃዎች

አንድ፦የኢሕአዴግን አምባገነን አገዛዝን ከመንግስት ስልጣን በሕዝባዊ ተቃዉሞ ማስወገድ

ሲሆን፡ ይህን ለማስፈጸም የሚመሰረተዉ ሕብረት የአንድነት ሃይሎች ሕብረት ይሆናል።

ሁለት፦የሰዉ ልጅ እኩልነት በሁሉም አቅጣጫ የሰፈነባት፣ የሕግ የበላይነት የነገሰባት፣ የሕገመንግስት ዋስትና ያላት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መመስረት።

በዚሕ ደረጃ የሚኖረዉ ሕብረት ከበፊቱ የሰፋ፡ ነገር ግን የኢትዮጵያን አንድነት ቅድሚያ የሚሰጥ ይሆናል።

ታጠቅ ይህ ግልጽ የዓላማና የአፈጻጸም ቅደም ተከተልን ያቀፈ አስተሳሰብ፡ የምናልመዉን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር፡ በዛሬዉ የአገራችን ሁኔታ ብቸኛዉ መንገድ ነዉ ብሎ ያምናል።

የአንድነት ሃይሎችን ብቻ የሚያካትት ህብረት ለምን አስፈለገ?

ይህን አማራጭ ለመዉሰድ ብዙ ጉዳዮችን ወይም ምክንያቶችን ግንዛቤ ዉስጥ ከቶ ማየት ይሻል። ለምሳሌ፦የቅድሚያ ጥያቄ - ማለትም አሁን ባለዉ የኢትዮጵያ ተጨበጭ ሁኔታ ጸረ-ኢሕአዴግ የሆኑ ሃይሎችን በሙሉ የሚያካትት ሕብረት ነዉ ቅድሚያ የሚሰጠዉ ወይስ የአንድነት ሃይሎችን ብቻ የሚያካትት ህብረት?

ከእስትራተጂም ሆነ ከትግል ታክቲክ አንጻር ሲታይ ደግሞ በዓላማችን ላይ የተመሰረተ የአንድነትና የሌሎች ወገኖች ህብረት መመስረት ከቶዉን አስፈላጊ ነዉን? የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም ማስከበር የሚጀምረዉ መቼ ነዉ? አሁን ካለንበት የሃይልና የከባቢ ሁኔታ አንጻር ሲታይ ዘላቂዉን የአነድነት ሃይል ካሁኑ ቅድሚያ አለመስጠት ጎጂ ሊሆን አይችልምን? ሗላ ይምጣ ቢባልስ አይዘገይምን? የሚሉት ጥያቄዊች፡ መመለስ አለባቸው።

ዛሬ ያለንበትን ሁኔታ - ከሰዉ ሃይል እሰከ ማቴሪያል አቅም፣ የአደረጃጀታችን ጥንካሬ፤ የዓለም አቀፍ ድጋፍ፣ የጎረቤት አገሮች ሁኔታ፣ እርስ በርስ ያለን መደጋገፍ ወይ መነቃቀፍ፣ ወዘተረፈ- የተገንጣይ ሃይሎችን ይዞታና ጥንካሬ አካቶ መመልከት የግድ ነዉ።

ሕብረታችን ተገንጣይ የሚባሉትን ድርጅቶች ይቀፍ ወይም የአንድነት ሃይሎች ሕብረት እነሱን አግልሎ አይመስረት ወዘተ. የሚሉ ወገኖች የሚያቀርቡትን ነጥቦች እስቲ እንመልከት። በኢትዮጵያዊነታቸዉ የማያምኑ አንዳንድ ድርጅቶች ሁኔታዎች ከተስተካከሉላቸዉ አቋማቸዉ የበለጠ ወደ አንድነት ሊያዘነብል ይችላል ይላሉ። ማለትም የብሄረሰብ መብቶች ሙሉ በሙሉ ከተከበሩላቸዉ፣ ወዘተ.- አንድነት ዉስጥ መጠቃለል የሚፈልጉ ስለሆነ አሁን ‘ተገንጣይ’ ልንላቸዉ አይገባም፤እንደ ወገን አይተናቸዉ አብረናቸዉ ብንሰራ በሂደት ልንቀይራቸዉ እንችላለን የሚል ነዉ። ከዚሁ ጋር የተዛመደ ሌላዉ አስተሳሰብ ደግሞ - ተገንጣይ ይባሉ የነበሩ ድርጅቶች አሁን በአንድነት ስር በሚካተቱና አንድነትን በማይፈልጉ መሐል ተከፋፍለዉ ስለሚገኙ በደፈናዉ‘ተገንጣይ’ ልንላቸዉ አይገባም የሚል ነዉ። (ይህ እዉነት ከሆነ የሚጠላ የለም!) በተጨማሪ በአገሪቱ፡ የ”አረቡ ፀደይ፡ (The Arab Spring) ሁኔታ በቅርቡ ማጋጠሙ አይቀርምና፡ ቅድሚያ እኒህን ‘ተገንጣይ’ ተብለዉ ከሚጠሩት ሃይሎች ጋር በመቀራረብ ማረጋጋት፤ ከተቻለም በጋራ ትግል ኢሕአዴግን ማስወገድ አለብን የሚል ነዉ።

በተለይ ግንቦት 7ን ብንወስድ፡ በተገንጣይነት የሚነገርላቸዉን ድርጅቶች እንደማንኛዉም አባል ድርጅትነት በሕብረት ተካተዉ፡ የጋራ ትግል በማድረግ የኢሕአዴግን መንግስት ከመንግስት ስልጣን ከገለበጥን በሗላ፡ በነጻነት የፖለቲካ ከባቢ ሕዝቡ ነጻ ዉሳኔ ላይ እንዲደርስ ይደረጋል - በትግሉም ሂደት ዉስጥ የመገንጠል አዝማሚያ ያለቸዉን ወገኖች ሃሳባቸዉን እንዲቀይሩ ማድረግ ይቻላል - ሌላ አማራጭም የለም ይላሉ።

አንዳንድ ተቃዋሚ ምሁራንም ከግንቦት 7 አቋም ባልተለየ መንገድ ከላይ እንደተጠቀሰዉ ‘ተገንጣይ’ ይባሉ የነበሩ ድርጅቶች ሁኔታዎች ከተደላደሉላቸዉ- ኢትዮጵያዊነታቸዉን ሊቀበሉ ስለሚችሉ አሁን ‘ተገንጣይ’ በማለት ልናገላቸዉ አይገባም፤እንደ ወገን አይተናቸዉ አብረናቸዉ ብንሰራ በሂደት ልንቀይራቸዉ እንችላለን። ወይም ደግሞ ተገንጣይ ይባሉ የነበሩ ድርጅቶች አሁን በአንድነት ስር በሚካተቱና አንድነትን በማይፈልጉ መሐል ተከፋፍለዉ ስለሚገኙ በደፈናዉ‘ተገንጣይ’ ልንላቸዉ አይገባም ይላሉ።የጊዜዉን የኢትዮጵያ ሁኔታ በመገምገም ደግሞ እኒሁ ምሁራኖች አሁን ያለንበት ሁኔታ የብሔር/ብሔረሰብ ድርጅቶች ያየሉበትና የአንድነት ሃየሎች የፈዘዙበት ወይም የደከሙበት ጊዜ ስለሆነ በቅርብ ጊዜም ሊፈነዳ የሚችል የሕዝብ አመጽን ያዘለ ሁኔታ ስላለ ከብሔረሰቦች ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመስራት መሞከር ቅድሚያ ሊሰጠዉ ይገባል ይላሉ።ኢትዮጵያ እንደ አንድ አገር የመቀጠል ያላት ዕድል ከተገንጣዮቹ ጋር መስራት ከቻልን፣ ቅድሚያ ለዚህ ሰጥተን ከሰራን ነዉ ይላሉ።

በተቃራኒዉ ደግሞ ታጠቅን ጨምሮ ያለዉን አቋም ብንወስድ፡ አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት የፖለቲካ ቀዉስና አንድነት የመፍረስ ሁኔታ አንጻር፤ ቅድሚያ የሚሰጠዉ ጉዳይ፣ የአንድነት ሃይሎችን ማሰባሰብ ነዉ - ተገንጣይ ሃይሎችን በመጀመሪያዉ ትግል በማሳተፍ ላይ ጊዜና ገንዘብ ሊባክን አይገባም የሚል ነዉ። ከዚህም ባሻገር ከተገንጣዮች ጋር አብሮ መሰለፍ የሚለዉ ጉዳይ ከበፊት ልምዳችንና ከላዕላይ-ዓላማችን አንጻር ሲታይ ለአገራችን አደጋ ሊሆን ስለሚችል ትብብር እንኳ ቢኖር ተገንጣዮችን እስካላጠናከረ ድረስ መሆን አለበት የሚል ነዉ።

እነዚህ ተገንጣይ ብለን የምናዉቃቸዉ ድርጅቶች ነገ ሁኔታ ሲቀያየር ወደ አንድነት ሊሳቡ ይችላሉ ብሎ ማሰብ መልካም ነዉ። ጥያቄዉ ግን ዛሬ ምን እናድርግ ነዉ?

ስለዚህም ዛሬ ቅድሚያ የሚሰጠዉ ጉዳይ የቱ ነዉ ብለን ስንጠይቅ፦

 1. አገሪቱ በጎጥ አስተሳሰብ በተጠመቀ አገዛዝና ከፋፍለሕ ግዛ መርህ የምትመራበትና ይህም በተወሰነ ደረጃ የሕዝቡን አንድነት የሸረሸረበት ወቅት በመሆኑ፤

 2. የቆየ የመገነጠል ዓላማ ያነገቡ የብሄር ድርጅቶች በትጋት ዕድላቸዉን በመጠባበቅ ላይ ያሉበት ወቅት በመሆኑ፡

 3. እኒሁ የብሔር ድርጅቶች ከአካባቢ ጸረ-ኢትዮጵያ መንግስታት ጋር በመሻረክ የ’አንድነት ሃይሎች’፡ ተብለዉ ከሚጠሩ ድርጅቶች የተሻለ የገንዘብና የትጥቅ ይዞታ ማደራጀት ስለቻሉ፤

 4. በተለይ በአንዳንድ ክልላት፡ የአለም አቀፍ ትኩረትን የጣለ ማእድናት መገኘታቸዉ ኢትዮጵያን አፈራርሰዉ ተጠቃሚ ለመሆን የሚጓጉ ሃያላን አገራት በመከሰታቸዉ

አገራችን ከፍተኛ የመከፋፈል አደጋ ላይ ናት። በመሆኗም በብዙሃኑ የአንድነት ሃይሎች አስተሳሰብ ቅድሚያ የአንድነት ሃይሎችን ማደራጀት ያደርገዋል።

ደግሞ የብሔር/ብሔረሰብ ድርጅቶች በአሁኑ ሰዓት ያይሉ አያይሉ፣ በቅርብ ጊዜም ሊፈነዳ የሚችል የሕዝብ አመጽ ይኑር አይኑር፤ የአንድነት ሃይሉ ባስቸኳይ እራሱን አዘጋጅቶ በደረሰበት የአቀም ደረጃ የሚገጥመዉን ትግል ለመቋቋም መጣር ይኖርበታል- ቅድሚያ ሊሰጠዉ የሚገባዉ ጉዳይ የአንድነት ሃይሉን (ማለትም በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት የሚያምነዉን ክፍል) ማጠናከር ነዉ። ይህ አቋማችንን ጥር 24 2002 በወጣዉ መግለጫችንም ግልጽ ሆኖ ነበር፦

“ታጠቅ ለነጻይቱ ኢትዮጵያ፤ጽ/ቤታቸዉን ከአገር ዉጭ ያደረጉ፤ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መስፈን እና ሉዓላዊ አንድነቷ መከበር የሚያምኑ ተቃዋሚ ድርጅቶች በሙሉ የሚሰባሰቡበት መድረክ ለመፍጠር የመንደርደሪያ ስብሰባ እንዲጠራ ጥሪዉን ያደርጋል”

ስንል አቋማችንን ግልጽ አድርገናል።

ዛሬም በአሁኑ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ፣ የአገር አንድነት ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠዉ ይገባል፣ መንገዱም የአንድነት ሃይሎችን ባስቸኳይ ሕብረት እንዲመሰርቱ ማድረግ ነዉ - በማለት ከዚህ አኳያ ከሌሎች የአንድነት ሓይሎች ጋር ሕብረትን ለማደራጀት ታጠቅ ጥረት እያደረገ ነዉ።መንገዳችንም ትክክለኛና በሕዝባችንም ዘንድ ተቀባይነት ያለዉ በመሆኑ ለድል እንደሚያበቃን አንጠራጠርም።

የአደራ መልዕክት ለወጣቱ ትዉልድ

በተለይ ወጣቱ ትዉልድ በጊዜ ሊገነዘበዉ የሚገባዉ ጉዳይ፡ ይህ ኢትዮጵያን የማፍረስ ጥቃት በኢትዮጵያ ላይ ሲዘነዘርባት፡ የመጀመሪያዉ እንዳልሆነና የመጨረሻዉም እንደማይሆን ነዉ። ስለዚህም ሁልጊዜ ነቅቶ የመጠበቅ ግዳጅ አለበት። በረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ እንደተዘገበዉ የአገሪቱን አንድነት የተፈታተኑ የተለያየ ቅርጽና ይዘት ያላቸዉ ወገኖች ተከስተዉ ነበረ። በየጊዜዉም ልዩነቶችን በማቻቻል ይሁን ወይ ባንዱ ወገን የበላይነት ታላቅ ባለታሪክ አገር ይዞ መቆየት ተችሏል። ዘመናችን ከበፊቱ ዘመናት እጅጉን ተቀይሯል።ቢሆንም ግን በአገራችን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት አለመስፈኑን ምክንያት በማድረግ ትግላቸዉንና ዕድላቸዉን ከተቀረዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ለማድረግ የማይፈልጉ፤ አንዳንዶች ደግሞ፡ ኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ሆነች አልሆነች የቆየ የመገንጠል ዓላማቸዉን ብቻ ማሳካት የሚፈልጉ ወገኖች በመኖራቸዉ የተወሳሰበ ሁኔታ ዉስጥ የመግባትና የመፈራረስ አደገ ላይ ወድቀን እንገኛለን። ስለዚህም በአንድ ወገን የበላይነት ሳይሆን በመላ ሕዝቦቿ ዴሞክራሲያዊ እኩል ተሳታፊነት ይችን ታላቅ ሃገር ይዘህ ወደ 21ኛዉ ምዕተ ዓማት መዝለቅ ትችላለህ ወይ? የሚል ፈተና ቀርቦልሃል!

የወደፊቷ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ይዞታ እንደሚኖራት የራሷ፤የከባቢዋና የዓለም አቀፍ ይዞታዉ የሚያስገድዳት ቢሆንም እንደ አንድ ሉአላዊ አገር ሆነን የመዝለቅ ጥያቄዉ የሚጸናዉ ግን በአንተ ቆራጥ የአንድነት አቋምና መስዋዕትነት ብቻ ነዉ። ለአንድነት የምታደርገዉ ትግል የመጀመሪያዉን ፈተና የሚያልፈዉ የአንድነት ሃይሎችን ጠንካራ ሕብረት የመሰረትክ/የመሰረትሽ ጊዜ ነዉ።

ይህንንም ስንል፡ የአንድነት ሃይሎች የመገንጠል ዓላማ ካላቸዉ ድርጅቶች ጋር ምንም ግንኙነት ሊኖራቸዉ አይገባም ማለታችን አይደለም። በተቃራኒዉ እነሱን ሊያጓጓ፣ ሊስብ የሚችል ህብረት እንመስርት ነዉ ያልነዉ እንጂ፡ ከሕወሀት/ኢህአዴግ ስልጣን መያዝ በፊት አንዳዶቻችን ከተገንጣይ ድርጅቶች ጋር የጀመርነዉ መነጋገርና መቀራረብ ይቅር ማለት አይደለም። ባይሆን ከነሱ ጋር ያለን ግንኙነት የኢትዮጵያ አንድነት ይዞታን ዝቅ በማድረግ የመገነጣጠልን ሁኔታ የሚያጎላ ማናቸዉንም እንቅስቃሴ ዉስጥ ከመግባት መቆጠብ ይኖርብናል እንጂ። ለምሳሌ የመገንጠል ዓላማ ካላቸዉ ድርጅቶች ጋር ለኢትዮጵያ አንድነት ከአሁን በሗላ እንደሚቆሙ አንድ አይነት ዉል ላይ ሳይደረስ ወይም ሌላ መሰረት ያለዉ ነገር ሳይገኝ ወይም ይህን የሚያረጋግጥ አቅጣጫ ሳይያዝ ሕዝባዊ ስብሰባዎች እየጠሩ ለዳያስፖራዉ ብቻ ሳይሆን ለዉጩ ሕብረተሰብ ማስተዋወቅ የአንድነትን ትግል ያዳክማል እንላለን። ከዚህም በፊት በደርግ ጊዜ ተመሳሳይ ስራ ተሰርቶም ከሆነ ጥፋት ነበረ ፤ ከዚህም ዛሬ መማር ነዉር አይደለም። በአጭሩ የተገንጣይ ድርጅቶችን ለመመለስ የሚደረገዉ ጥረት የኢትዮጵያን አንድነት በሚያንኳስስ ደረጃ እስካልሆነ፡ በጥንቃቄ እስከተደረገ ድረስ፡ ተቃዉሞ የለንም።

የአንድነት ሃይል መጠንከር፡-

 1. ሕዝባችን በአገር ቤት በአንድነት የበለጠ እንዲጠነክር ያደርገዋል፣ እነደግብጽ የሕዝብ አመጽ ቢከሰት ሕዝቡ ለአንድነትና በአንድነት መንፈስ እንዲበረታታ/እንዲጸና አስተወጽኦ ያደርጋል

 2. ዳያስፖራዉ ሕብረተሰብ ከቅንጅት ጊዜ በበለጠ በአንድነትና በብዛት እንዲቆም፤ በዚህም ምክንያት የምዕራቡ ዓለም ወደደም ጠላም የሚያዳምጠን ሁኔታን ይፈጥራል

 3. ይህ በመሆኑም የመገንጠል ሃሳብ ያላቸዉ ድርጅቶች በሕዝባችንም ሆነ በዓለም አቀፍ ሕበረተሰብ ተቀባይነታቸዉ ደካማ ስለሚሆን በአንድነት ጎራ ዉስጥ የመካተቱን ሃሳብ እንዲያውጠነጥኑ ያስገድዳቸዋል

 4. በራስ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ መተማመንን ስለሚፈጥር ለአንድነት ሃይሉ አስፈላጊ ሆኖ ከታየዉ የመገንጠል ሃሳብ ካላቸዉ ድርጅቶች ጋር ትብብር መፍጠር ያስችለዋል።

በማጠቃለል ዛሬ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በተቃዋሚዎች የቀረበለት አማራጭ ግልጽ ሊሆን ይገባል። የሚወስነዉም ዉሳኔ የትግል አሰላለፉን የሚተልምና የኢትዮጵያንም የወደፊት ዕጣ የሚያንጸባርቅ ነዉ። ዛሬ ለሕዝባችን የቀረበለት አማራጭ ከመቸዉም ጊዜ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። በተለይ የአረቡ ጸደይ፡ የአፍሪካ ጸደይ ሆኖ በሚከሰትበት ጊዜ፡ ለምን መቆም እንዳለብን ከወዲሁ ቁልጭ ብሎ መታየት ይኖርበታል። አዲሰ ነገር መፍጠር ሳይሆን የሕዝቡን ፍላጎት በማያሻማ መንገድ ማስቀመጥ ይኖርብናል። ይህም በአጭሩ ከወደፊታችን የሚደረገዉ ተጋድሎ ለዲሞክራሲ ብቻ እንዳልሆነና ኢሕአዴግ የሸረሸረዉን የሕዝባችንን አንድነትም መልሰን ለመትከል እንጂ።

የድርጅቶች አንድ ላይ መቆም ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ስንል እንጂ ኢሕአዴግን ለመገርሰስ ብቻ እንዳልሆነ ላንዴም ለመጨረሻ ጊዜም ግልጽ መሆን ይኖርበታል። በዚህም የሚያምኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር ለመስራት ታጠቅ ከመቸዉም ጊዜ በበለጠ ዝግጁ ነዉ።

ቅድሚያ ሕብረት በዴሞክራሲያዊ አንድነት ለሚያምኑ ሃይሎች ይሁን!

እሰክንድር ነጋና ሌሎች የሙያ ሰዎች እንዲሁም የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ይፈቱ!

ኢትዮጵያ ለዘልዓለም ትኑር!