በእናት አይንና በንስር አይን፡ የብርቱካን መፈታት


የ”ሞራል” ብቃትና የሞራል እጥረት፡ ለነገሩ የተፈታው ማነው? እንዳጋጣሚ ሆኖ፡ ብርቱካንን ለመገምገምና በብርቱካን ላይ የ”ሞራል” ብያኔ ለመስጠት የሚያስችል የ”ሞራል” ብቃት የለኝም። ግን እንደ ባህል፡ ይሄ “አንተ ወይም አንቺ ይሄንን ለማለት ወይም እንዲህ ለመናገር፡ የሞራል ብቃት የለህም/ የለሽም” የሚል መፈክር ደሜን ያፈላዋል። ፖለቲከኞች ላይ የሞራል ፍርድ ለመስጠት የሞራል ብቃት አያስፈልግም። ፖለቲከኞችና ስራቸው እንደ መርህ ለማናቸውም ግምገማና ፍርድ የተጋለጡ ናቸው። ኦባማንና አስተዳደሩን ለመገምገም የአሜሪካ ህዝብ የተለየ የሞራል ብቃት አያስፈልገውም። መንጌ፡ ሃራሬ ቤቱ ቁጭ ብሎ፡ እሱ የሰራውን ቢሆንም እንኩዋን የሚደግመው፡ መለስን መገምገምና ማብጠልጠል ይችላል። ብርቱካንንና ፖለቲካዊ እርምጃዋን ለመገምገም፡ የግድ ለቅጽበትም ቢሆን በቃሊቲ መታሸት የለብንም። በቂ ምክንያት እስካለና፡ በቅን ልቡና እስከተነሳሳን ድረስ፡ የፖለቲካ መሪዎችን መገምገም መብት ነው። እነሆ ከብርቱካን ጉዳይ ጋር በተያያዘ መብቴን ልጠቀም ነው። እንዳጋጣሚ ሆኖ ግን በበጎ ነው።

ባለፈው እሁድ የተቀዳ የአዲስ ድምጽ ሬዲዮ ዝግጅት ላይ፡ አንድ አድማጭ ስለብርቱካን መፈታት በሰጡት አስተያየት፡ “የተፈታችው ብርቱካን አይደለችም? የተፈታው መለስ ነው”። እውነት ነው። እንዳትፈታ ባልጸልይም፡ አንዳንዶች “ይድፋህ” እያሉኝም ቢሆን፡ ለትግላችን የሚጠቅመው ብርቱካን ባትፈታ እንደነበር በጻፍኩ በጥቂት ቀናት ውስጥ ብርቱካን ተፈታች። ማለቴ፡ መለስ ተገላገለ። በኛ በተቃዋሚዎች እየተሳለቀም ቢሆን፡ በብርቱካን መፈታት ሕወሀት/ኢህአዴግ እፎይ እንዳለ ለኢህአዴግ ቅርብ የሆነው ኢትዮጵያን ሪፖርተር ጽፏል። በዚህች ምስኪን ሴት እንግልት ማብቃትና፡ በኚያ አረጋዊ እናቷ መከራ ማጠር፡ እንዲሁም በከፊልም ቢሆን ድል ስላደረግን ተደሰትኩ። ግን ደግሞ፡ በብርቱካን መፈታት በደስታ ዘልዬ ብቻ ማቆም አልፈቀድኩም። ይሄ ጽሁፍ ስለብርቱካን መፈታትና በፖለቲካችን ላይ ስለሚያሳድረው አሉታዊ ተጽእኖ የሚያትት ነው። ይሄ የማይመቸው፡ ብዙ ድረ ገጽ ሳያጣብብ፡ ጊዜውን ሳይገድል፡ እኔንም ብዙ ርግማን ሳያሸክመኝ፡ ለኔም ለሱም ደህንነት ሲል፡ ከዚህ የክርክር ሰረገላ እዚሁ ይውረድ።

ስንደግፍ መቶ ከመቶ፡ ስንቃወም መቶ ከመቶ

ብርቱካን ላይ ምንም አይነት የሞራል ግምገማና ሂስ ለመስጠት እንደማልደፍር ተናግሬያለሁ። ባደርገውም እንኩዋን፡ ማንም እንዳይፈረድበት አይፍረድ፡ ደግሞም እሱ ባማይዳኝበት ህግ አይዳኝ ተብሎ በማላስታውሰው መጽሀፍ ተጽፏልና ተጠንቅቄ ነው። ግን ደግሞ ብርቱካን የኔ ብጤ ተራ ሰው አይደለችም። ብርቱካንን እንደ ተራም ሰው ይሁን እንደ ታላቅ መሪ ከገመገምኳት፡ ያደረገችውና የምታደርገው ሁሉ እጹብ ድንቅ ነው። ብርቱካንንና ስራዋን እንደፖለቲከኛ ስገመግም ግን ለራሴም የማላነሳውን ጥያቄ ላነሳ፡ ለራሴም የማልጠቀመውን ሚዛን ልጠቀም እችላለሁ። ምክንያቱም እኔ እሷ የተመኘችውን ወይንም የምትመኘውን ሕይወት አልኖርምና። በሌላ አነጋገር፡ መሪዬን የምገመግመው፡ እኔን ከምገመግምበት በተሻለ መመዘኛ ነው እንጂ፡ በኔ አይነት ሚዛን አይደለም። ስለዚህም፡ ብርቱካን ላይ ምንም አይነት የሞራል ፍርድ ሳንሰጥ፡ ነገር ግን የብርቱካን መፈታት በፖለቲካችንና በትግላችን ላይ ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ተጽእሎ ማስረዳት እወዳለሁ። የብርቱካን መፈታት፡ እንደ ተራ እስረኛ ካየነው፡ ደስ የሚያሰኝ፡ እንደ ፖለቲከኛና እንደ መጪው ትውልድ መሪ ስንመለከትነው ግን ከደስታችን ጎን ለጎን በጥንቃቄ ልንመለከተው የሚገባ ክስተት ነው።

የብርቱካን መፈታት ቢያስደስተንም፡ በቅጥ ልናጤነው የሚገባ አደገኛ ጎንም አለው ብዬ እንድጽፍ ያነሳሳኝ ብዙ ምክንያት አለ። አንደኛ ነገር፡ ጎዶሎ ትጥቅ ይዞ ከመገስገስ፡ ያንድን ጉዳይ አሉታዊ ጎንም ማንሳት ትግላችንን፡ አመለካከታችንን፡ አቋማችንን ሙሉ ያደርገዋል እንጂ ጎጂ አይደለም ከሚል ምክንያት ነው። በኛ አገር የድጋፍና የተቃውሞ፡ የሀዘንን የደስታ ባህል ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር፡ ስንደሰት መቶ ከመቶ፡ ስናዝንም መቶ ከመቶ፡ ስንደግፍም መቶ ከመቶ፡ ስንቃወምም መቶ ከሞተ ነው። ምሳሌ፡ ዶ/ር ብርሀኑን የሚደግፉ ሰዎች በምንም መልኩ ዶ/ር ብርሀኑ እንዲተች አይፈልጉም፡ አቶ ሀይሉ ሻውልን የሚከተሉ ሰዎችም አቶ ሀይሉ ሻውል ሲነኩ ያማቸዋል። ይሄንን ሁሉ የማትተው ለምንድር ነው፤ የብርቱካንን መፈታት ተከትሎ የሚጎርፈው ደስታና አድናቆት፡ አንዳንድ አስፈላጊና ጠቃሚ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን እንዳናይ ሊያውረን ይችላል ብዬ ስላሰብኩ፡ ከብዙሀኑ ደስታና ድጋፍ በተለየ መልኩ የለም መፈታቷ ይሄ አይነት ጉዳትና አደጋም አለው፡ ስለዚህ ስንደሰት፡ በጥንቃቄ ይሁን ለማለት ነው። ብርቱካን መፈታቷ አደጋ አለው ማለት፡ ብርቱካን ታስራ ይቅር ማለት ሳይሆን፡ በመፈታቷ ሊኖር የሚችለውን ክፍተትም አስበን፡ ያንን ክፍተት ለመሙላት እንዘጋጅ ለማለት ነው፡ እንጂ፡ ብርቱካን ብቻዋን የዚህን ህዝብ ቀንበር እንድትሸከም ለመፍረድ አይደለም። የብርቱካን መፈታት የሚያስደስት ቢሆንም፡ በሌሎች እስረኞችና በትግላችን ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራለ ከሚለው ትችት ግን አያመልጥም።

ኢህአዴግ/ሕወሀት እናዳሰበው እንዳንሆን ሳስብ

ፈረንጆቹ ራሳቸው፡ የብርቱካንን መፈታት በጥርጣሬ ነው የሚመለከቱት። አስተሳሰሯም አፈታቷም በርግጥም ህግን ሳይሆን የስርአቱን ስርአተ አልበኝነት ነው መሰረት ያደረገው። ስለዚህም የብርቱካንን መፈታት ተከትሎ፡ ልክ እኛ ኢትዮጵያዊያኑ እንዳሳየነው ያልተገደበ ጮቤ መርገጥ ሳይሆን፡ የተለያዩ አለምአቀፍ ድርጅቶች ጥንቃቄ የተሞላባቸው መግለጫዎችን ነው ያወጡት። ምእራባዊያን ራሳቸው፡ የኢህአዴግ/ሕወሀትን ገገማነት ነቅተውበታል። ለምሳሌ የአምሮፓ ህብረት ተወካይ፡ በምንም መልኩ የብርቱካንን መፈታት እንደ ሀቀኛ የይቅርታ ሂደት አልተመለከተውም። የውጭ ግንኙነት ሀላፊዋ “ብርቱካን በአገሪቱ ህግ መሰረት ይቅርታ ባገኘችበት መልኩ የተጠናቀቀውን ሽማግሎች ያቀነባበሩት የኢትዮጵያ ባህላዊ የፍትህ ስርአት ስለተጠናቀቀ እንኳን ደስ አላችሁ። የአውሮፓ ህበርት ብርቱካን እንድትፈታ አበክሮ ሲታገል ነበር።” ብሎ ነው ያስቀመጠው። ይሄ ህዝቡን አጭበርብራ፡ የውጭ መንግስታት ያድኑኛል ብላ ገነመሌ የሚለውን መደዴ ነገር ዞር ብለውም አላዩትም። http://www.consilium.europa.eu/uedocs/cms_data/docs/pressdata/EN/foraff/116917.pdf

የታይም መጽሄት ጸሀፊ ደግሞ “የብርቱካን መፈታት የምር ነው ወይንስ የታይታ” ሲል የኢህአዴግን አሰራር በደንብ የበለተ ረጅም ሀተታ ጽፈል። http://www.time.com/time/world/article/0,8599,2024273,00.html?xid=rss-fullworld-yahoo ፤ ከሂውመን ራይትስ ወች ፡ http://ethiomedia.com/augur/3963.html እስከ አምነስቲ አለማቀፍ፡ ከመኢአድ እስከ ሶሊዳሪቲ፡ የኢህአዴግን ገገማ መግለጫ ከቁብ የቆጠረው የለም። የአውሮፓ ፓርላማ አባልና፡ የምርጫ 2005 የአውሮፓ መንግስት ታዛቢ ልኡካን መሪ፡ ወ/ሮ አና ጎሜዝም፡ ከብርቱካን መፈታት በኋላ በላኩት አጭር ማስጠንቀቂያ አዘል መልእክት ትግላችን ገና እንዳላበቃ ገልጸዋል። ከብርቱካን መታሰር ጋር በተያያዘ፡ ከኛ ይልቅ ፈረንጆቹ ተጠንቅቀው ነው የተደሰቱት። ወ/ሮ አና፡ “የብርቱካንን መፈታት መልካም ዜና ተከትሎ አሁንም ብርቱካን ራሷንም ሌሎችንም የኅሊና/ፖለቲካ እስረኞችንም ወክላ የሳካሮቭን ሽልማት እንድትቀበል ዘመቻችንን መቀጠል አለብን” ብለዋል። http://www.europarl.europa.eu/members/public/geoSearch.do;jsessionid=6BF592FD6F71C497D2C0347AADBF4906.node2?language=en).

የብርቱካንን መፈታት በብርቱካን እናት አይን አላየውም

ብርቱካን ከተፈታች ገና ጥቂት ቀኗ ነው። ስለቀጣይ የፖለቲካ ሕይወቷ ያለችው፡ ወይም የሰጠችው ፍንጭ የለም። የሰማናቸው ጥቃቅን ቃለ ምልልሶችና ያየናቸው ቁርጥራጭ የቪዲዮ ምስሎች፤ ብርቱካን ያሳለፈችውን አስቸጋሪ ሁኔታ ሲጠቁሙ፡ የብርቱካንን ቀጣይ ፖለቲካዊ ጉዞ አይናገሩም። አሁን ዘግይቶ በደረሰን መግለጫዋም፡ ጠንቃቃና ስለቀጣይ ፖለቲካዊ ጉዞዋ ውሳኔዋን ለማሳወቅ ተጨማሪ የጥናት ጊዜ የምትጠይቅ ትመስላለች። በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ የሚሆነውን እንመለከታለን። http://addisnegeronline.com/2010/10/birtukan-taking-%E2%80%9Ctime-to-reflect%E2%80%9D/ ስለዚህ፡ የብርቱካን ጉዳይ ላይ፡ ጠንካራና ርግጠኛነት ያለበት አስተያየት ለመስጠት፡ ተጨማሪ ጥቂት ቀናት መጠበቅና፡ የሷን ውሳኔ መስማት አለብን። የሆነ ሆኖ ግን እስከዚያው፡ ከእስካሁኑ ሕይወቷ ላይ ተነስተን፡ መፈታቷን ተከትሎ የተሰጠውን የሰዉን አስተያየትና መግለጫ አስታከን፡ የሚከተለውን አስተያየት መስጠት ይቻላል።

እኔና ብርቱካን፡ እናቷና እሷ፡ እሷና ልጇ፡ እሷና ቤተሰቦቿ እንዳላቻው አይነት የስጋ ልደት የለንም። የኔና የብርቱካን ዝምድና የፖለቲካ ነው። የሆነ ሰዓት ላይ እኔም የምጋራውን የፖለቲካ አመለካከት ማራመድ፡ ማራመድም ብቻ አይደለም ይዛ መታገል ስለጀመረች፡ በዚያም ብርቱካን ነጻነቴን ልታመጣ የምትታገል ጀግና ሆና ስላገኘኋት ተዛመድኳት። ስለዚህ፡ ዝምድናችን የስጋ ቢሆን፡ ልክ እንደናቷ፡ “መንግስትንም፡ እግዚአብሄርንም፡ ህዝቡንም፡ አመስግኘ ስለተፈታችልኝ ደስ እንዳለኝ ገልጬ” አልፍ ነበር። የብርቱካንና የኔ ዝምድና ግን የፖለቲካ ስለሆነ፡ የብርቱካንን መፈታት በፖለቲካ መነጽር ነው የምመለከተው። ብርቱካን መፈታቷ ባንድ በኩል ደስ ቢልም፡ በትንሹም ቢሆን በፖለቲካ ያከሰረን ነው ባይ ነኝ። (ቆይ፤ ተረጋጉ፡ ለመሳደብ እንዳትቸኩሉ።) ልብ አድርጉ፡ በምንም መልኩ ብርቱካንን ለዚህ ኪሳራ ተጠያቂ እያደረግኩ አይደለም። ብርቱካን ለመታሰሯ ጥፋት እንደሌለባት ሁሉ፡ የተፈታችበት ሁኔታም የሷ ጥፋት አይደለም። በመፈታቷ ለመደሰት የተዘጋጁ ሁሉ ግን፡ መፈታቷ የሚያመጣውን ማናቸውንም ኪሳራም ለመጋፈጥ መዘጋጀት አለብን ለማለት ነው። የብርቱካን መፈታት፡ በተለይ ለምእራባዊያን መንግስታት፡ በምንም መልኩ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ እንዳለ እንዳይጠቁም፡ የፖለቲካ እስረኞችም እንደሌሉ እንዳይጠቁም መጠንቀቅ አለብን።

ይሄንን ሀሳቤን በምንም መልኩ እንደ ግለሰባዊ ጉዳይ አትመልከቱት። በብርቱካን መፈታት የምንደሰት ሰዎች ሁሉ ግን መፈታቷ የሚኖረውን ፖለቲካዊ አደጋም ማየት ካልቻልንና ከዚያ አደጋ አንጻር ተዘጋጅተን ካላጠቃን ወይንም ካልተከላከልን፡ አሁንም ጠላት ይበልጠናል ማለት ነው። የብርቱካን መፈታቷ፡ ከማንም በላይ ለኢህአዴግ መንግስት ትልቅ ትርፍ ነው። ኢህአዴግ/ሕወሀት ጥሩ መነገጃ ሊያደርገው ይችላል። ከዚህ ቀደም እንደገለጽኩት፡ http://ecadforum.com/files/batfeta-yshalal.pdf ፡ http://ethiomedia.com/augur/metaserwa_bejje.pdf ስርአቱ በዚህ እርምጃው፡ በአለም መንግስታት ዘንድ በኢትዮጵያ ውስጥ በርግጥም ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት እየሞከረ እንደሆነ ሊታይ ይችላል። ይሄ በራሱ በቂ ምክንያት ባይሆንም፡ የአሜሪካን ኤምባሲ፡ የብርቱካንን መፈታት ተከትሎ አወጣ የተባለው መግለጫ ይሄንን ይጠቁማል። የመግለጫውን ሙሉ ቃል ላገኝ አልቻልኩም። ኢትዮጵያን ሪፖርተር እንደዘገበው ግን፡ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ በወይዘሪት ብርቱካን መፈታትና ከቤተሰባቸውና ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር መቀላቀል የተሰማውን ደስታ ገልጾ፡ መፈታታቸው “መንግሥት ለመጪው ጊዜ ብሩህ ተስፋና ትኩረት መስጠቱን እንደሚያሳይ” ገልጿል ይላል። የብርቱካንን መፈታት ተከትሎ አንድ የሲያትል ነዋሪ እንደጻፈው፡ መለስ በኢትዮጵያ ውስጥ ፕሮፓጋንዳ ለሚነዛበት የአምስት አመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መስፈጸሚያ ብር ሊነግድበት ይችላል።

የብርቱካን ነጻነት የሌሎች አፈና መባሺያ ሊሆንም ይችላል

ለጋሽ መንግስታት በግልጽና እኛ በምንፈልገው ልክ ባያደርጉትም፡ ሰብአዊ መብት አያያዝንና ዴሞክራሲያውነትን እንደ አንድ የእርዳታ መመዘኛ ይወስዱታል። በዚህ ረገድ ላለፉት ሁለት አመታት ስለፖለቲካ እስረኞች ሲነሳ፡ የብርቱካን እስራት ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው አፈና ማሳያ ጥሩ ምሳሌ ነበር። ስለዚህ መለስ፡ ብርቱካንን በማሰሩ፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ እስረኞች እንዳሉ እንዳስመሰከረውና በሄደበት ሁሉ እንዳሰቃየነው ሁሉ፡ በብርቱካን መፍታትም፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተሻለ የፖለቲካ ነጻነት አለ ወይንም መንግስት የተሻለ ሁኔታ እንዲኖር ይጥራል የሚል እይታ ሊፈጥር ይችላል። በብርቱካን መፈታት መልካም ስም ማትረፍ ብቻ ሳይሆን፡ እንደውም፡ በብርቱካን ነጻ መለቀቅ ሽፋን፡ ሌሎች ስም የለሽ እስረኞች ላይ የሚደርሰው አፈናና ግርፋት ሁሉ ሊጨምር ይችላል።

በተራ ግለሰብና በፖለቲከኞች መካከል ያለን ልዩነት በደንብ ማጤን አለብን። የፖለቲከኞችና የተራ ግለሰቦች ስራ የሚመዘኑበትን ሚዛን የተለያየ ነው። እንኩዋንስ ፖለቲከኞች፡ ታዋቂ ሙዚቀኞች ወይንም ስፖርተኞች፡ ወይንም ባለሀብቶች እንኩዋን የሚለኩበት የሰብእና ሚዛን የተለያየ ነው። የብርቱካን መልካምም ይሁን መጥፎ ድርጊት ያንድ ተራ ሰው ድርጊት አይደለምና ባንድ ተራ ሰው ሚዛን አይመዘንም። የብርቱካን መፈታትም በኦነግነት ተጠርጥሮ፡ ወይንም በተቃዋሚነት ተፈርጆ የታሰረ አነድ ተራ እስረኛ መፈታት አይደለም። ከዚህ በኋላ የብርቱካን መፈታት በተወሰነም መልኩም ቢሆን በኢትዮጵያ ውስጥ የሌሎች የፖለቲካ እስረኞችን መኖር ሊከልለው ይችላል። ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ እስረኞች አሉ ብሎ ለማስረዳት ቀላል አይሆንም። ይሄንን የምለው፡ ለኔና ለናንተ አይደለም። ለሌሎች በየቀኑ በሰላማዊ ሰልፍ፡ በፒቲሽን፡ በረሀብ አድማ ለምንማልዳቸው ምእራባዊያን ሀይሎች ማለቴ ነው። ብርቱካን መደነቅ፡ መወደስ፡ ያለባት ታላቅ ሴት ነች። ሁሉም ነገር ግን እዚያ ጋር አያበቃም። የምናደንቃቸው ፖለቲከኞቻችን ስኬትና ውድቀት፡ ድልና ሽንፈት፡ እስራትና ነጻነት በትግላችን ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊም አዎንታዊም ተጽእኖ አለው። ስለዚህ ከአድናቆታችንና ከውዳሴያችን ቀጥሎ፡ የብርቱካንን ጉዳይ ከራሷም፡ ከብርቱካንም ከቤተሰቦቿም ባሻገር እንድንመነዝረው ፖለቲካችንና ትግላችን ግድ ይሏል። ብርቱካንን እያደነቅን፡ ጎን ለጎን ግን፡ በብርቱካን መፈታት የደረሰብንን ወይም የሚደርስብን ፖለቲካዊ ኪሳራ ለማካካስ ተግተን መስራት አለብን።

የምወደው በሱ ደስ የሚለኝ ጋዜጠኛ፡ ስለብርቱካን ሲናገር፡

የምወደው ጋዜጠኛ፡ የአዲስ አበባው እስክንድር ነጋ፡ ስለብርቱካን መፈታት ሲያትት፡ ብርቱካንን ለቅጽበት አግኝቻት፡ “አንቺ ለኛ ጀግና ነሽ፡ እኛም ዛሬ ኮራንብሽ” ባልኳት ግዜ፡ ሰዎች በዙሪያችን ስለነበሩ ልታወጣው አልቻለችም እንጂ፡ ጉሮሮዋ ላይ ተሰንቅሮ፡ ልውጣ አልውጣ እያለ የሚታገላት፡ እልህና ህመም አስተዋልኩባት ሲል ይጽፋል። ቀጠለናም፡ እስክንድር እንዲህ ሲል በብርቱካን አሳሪዎችና ፈቺዎች ድርጊት ላይ ቁጣውን ገለጸ። “ይሄ ይቅርታ አይደለም፡ ይሄ ራሳቸውም የጻፉትን ሕገ-መንግስት በሚቃረን መልኩ ሰውን ራሱን እንዲወነጅል የሚያስገድድ ውል ነው”። ታዋቂው የሕግ ባለሙያና መምህር፡ ዲባቶ አለማየሁ ገብረማሪያምም፡ የጎምቱውን ታጋይ ኔልሰን ማንዴላን “የሚደራደሩና የሚዋዋሉ ነጻ ሰዎች ናቸው፡ እስረኞች አይደሉም” የሚል ታዋቂ አባባል ጠቅሶ፡ ብርቱካንና “ይቅርታ ጠየቀች” የሚለውን ሀረግ አንድ ላይ አስቀምጠን እንዳንናገር፡ እንዳንጽፍ ያስጠነቅቀናል። እንደ እስክንድር አነጋገር፡ እነዚህ እንደጠላት የሚቆጥሩትን ሁሉ ለመደምሰስ የማይሳሱና ሀያ ዘመናት ያልተገደበ ስልጣን ይዘው ህዝብን ለማ

ጥፋት ደፋ ቀና የሚሉ አምባገነኖች፡ ሶስት ነገሮችን ለማድረግ ነው ብርቱካንን ያስፈረሟትና፡ የፈቷት። አንደኛ የብርቱካንን ሞራል ለመስበር፡ ሁለተኛ በብርቱካንና በደጋፊዎቿ፡ መካከል ልዩነትን ለመፍጠር፡ ሶስተኛ የዴሞክራሲ ታጋዩን ጎራ ሞራል ለመስበር። እነዚህ ነገሮች እንዲሳኩላቸው ያደረግን አንደሆነ ነው ኢህአዴግ ከብርቱካን እስር ሊያተርፍ የሚችለውና ሀሳቡ ሚሳካለት። ይሄ እንዳይሆን ተግተን መቆም አለብን ይላል እስክንድር። http://ethiomedia.com/augur/3968.html፡ የመላእክት አለቃ፡ ቅዱስ ሚካኤል ሁላችንም በያለንበት በጽናት እንቁም “ንቁም በበኅላዌነ እንዳለው” ማለት ነው። ትናንትም ትግል ላይ ነበርን: ዛሬም ትግላችንን እንቀጥላለን አይነት ነገር። ብርቱካን መፈታት ጋር የሚቆም ነገር የለም።

በርግጥም ብርቱካን ምንም ብላ ብትፈታ፡ በኛ ዘንድ ያላት ክብር ከቶም አይቀንስም። ሕወሀት እሷን ያዋረደ፡ እኛን ደግሞ አፍ ያስዘጋ መስሎት ያለፍላጎቷ የሚያስፈርማት ወረቀት፡ የሚያናግራት ይቅርታ፡ እኛ ስለብርቱካን ያለንን ግምት በምንም መልኩ አይለውጠውም። እንደውም የሕወሀት ስራ፡ ብርቱካንን እንደፖለቲከኛ ብቻ ሳይሆን፡ የሆነ እንደ አጥንታችን ክፋይ እንድናያት ያደርጋታል። በብርቱካን መፈታት ሰዎች ሁሉ፡ በተለይ ትናንት በጠላትነትም ተሰልፈውባት የተሰማቸውን ደስታ ሲገልጹ ስመለከት፡ ብርቱካን አይደለም ይቅርታ ጠይቃ፡ የአቶ መለስ ጫማ ስር ተደፍታ እየተንሰቀሰቀች ብትማጸንም፡ እኛ ስለብርቱካን ያለንን ክብርና ስሜት እንደማያጎድለው፡ እንዲያውም እልሀችንንና ቁጭታችንን እንደሚሰቅለው ዶ/ር ብርሀኑን ጨምሮ፡ ከብዙ ፖለቲከኞችና ፖለቲካ ተንታኞች ተረድቻለሁ። በዚህ ረገድ ወዳጄ ነአምን ዘለቀ የጻፈውንም ይመልከቱ። ያ ብቻም አይደለም፡ ያ ብርቱካን አለች ተብሎ በጽህፈትና በቴሌቪዥን ያየነውና፡ የሰማነው ጠላታችን ምን ያህ ርካሽና ጠባብ፡ መናኛና ወራዳ፡ ተራና ተርታ እንደሆነ አሳይቶናል። የሆነ ሆኖ፡ ኢህአዴግ/ሕወሀት ሊያሸንፍ የሚችለው እኛ እሱ እንዳሰበው ከሆንለት ነው። ምናልባት እስክንድር ካለው ላይ የምጨምረው ቢኖር፡ በብርቱካን መፈታት ተዘናግተን፡ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችን ከተውናቸው፡ ያኔ ጠላት የተመኘው ሆነ ማለት ነው። ስለዚህ በብርቱካን መፈታት እየተደሰትን፡ ጎን ለጎን ግን ጠላት ከዚህ እንዳያተርፍና ሌሎች እስረኞችም በዚህ ጭጋግ ውስጥ እንዳይረሱ መስራት አለብን። የብርቱካንን መፈታት በእናትና በስጋ ዘመድ አይን ብቻ ሳይሆን፡ በፖለቲካም አይን እንመልከተው ለማለት ነው። ግልጽ አይደለሁም መሰል? ይሄንን ማብራሪያ ለማብራራት ሌላ ማብራሪያ ስለምጽፍ፡ በሚቀጥለው ማብራሪያዬ እንገናኝ።

አለቃ ተክሌ ነኝ፡ ከቫንኩቨር-ኦታዋ፡ ካናዳ፡ ጥቅምት 2010

ለመላ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንክዋን ለ2003 አዲስ ዓመት አደረሰህ እንላለን! ለሕዝባችን ነጻነትና አንድነት እንመኛለን።

ለኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች በተጨማሪ እንክዋን ለኢድ አል ፈጥር አደረሳችሁ እንላለን!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!