እዉነት

እዉነትን፣ መከባበርን፣ይቅርባይነትንና፤ወንድማማችነትን እሴቷ ያደረገች

የታጠቅ ለነፃይቱ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ ልሳን

ሰኔ 2 2002

ቁ.1

ትግሉን ለማጠንከር በእዉነት መጀመር

የ2002 ምርጫ ተጭበረበረ፤ሰዉ ተገደል፤ ተደበደበ፤በዚህም ሁኔታ የምርጫዉ አሸናፊ ኢሕአዴግ ሆነ። እዉነተኛ አሸናፊዉን ግን ለማወቅ የምርጫዉ ዉጤት ተጠቃሚ ማን ነዉ? የሚለዉን ጥያቄ መጠይቅ ይኖርብናል።

በምርጫዉ ዉጤት ኢሕአዴግ ደነገጠ (“ሕዝቡ እንዴት ይወደኝ ነበር” አሉም ይባላል)። ተቃዋሚዉ ግን ተገረመ አዘነምም።

ኢሕአዴግ በ1997 ምርጫ የሕዝብ ድምጽ ሲነፈግ፣ “ጉድለቱን” ለማረም የማይደግፈዉ አብላጫ ሕዝብ ላይ የወሰዳቸዉ የድለላ፣የማስፈራራትና የጭቆና እርምጃዎች፣ ያለቅጥ በዝተዉ እራሱን ኢሕአዴግን ያስደነገጠ ተስፈንጣሪ ዉጤት ተከሰተ። በጠቅላይ ሚኒስቴሩ አነጋገር ኢሕአዴግ ከ “50-75% ድምጽ” እናመጣለን ብሎ ገምቶ ነበር። በሳቸዉም ሃሳብ በከፊል የተቃዋሚዉን ተሳትፎ ያቀፈ ፓርላማ ስለሚመሰርቱ፣የአለምን መንግስታትን ቡራኬ አገኛለሁ፤ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ አደረገ ተብዬ እመሰገናለሁ ብለዉ እንዳልተመኙ ሁሉ እንኻንስ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤እንኻንሰ የዓለም መንግስታት፤የኢሕአዴግ አባላት ጉድ የሚሉበት ምርጫ ሆነ። ኢሕአዴግ ባልጠበቀበት ሁኔታ ተጋለጠ። የኢሕአዴግ አምባገነንነትና ስርቆት በማያሻማ ሁኔታ ገሐድ ወጣ። ታዲያ የዚህ ምርጫ ተጠቃሚ ማን ነዉ?! እንዳለፈዉ ምርጫ ብዙ የደም ግብር ሳንከፍል በአለም ዘንድ ኢሕአዴግ ክፉኛ ሲጋለጭ፤ሳይተኩሱ መማረክ ይህ ነዉ ያሰኛል! የኢትዮጵያ ሕዘብና ተቃዋሚዉ ወገን የዚህ ምርጫ ተጠቃሚዎች ሆኑ።

ዛሬ ማዘን ያለበት በሕዝብ ላይ ያላግባብ ባደረገዉ ጭነትና ጭቆና እነዲሁም ማጭበርበር የተጋለጠዉ ኢሕአዴግ ነዉ። በምርጫዉ ማግስት የመለሰ ዜናዊን የተርበተበተ፣ የጥድፊያና የተማጽኖ ንግግር ላዳመጠ፤እንዲሁም በተከታታይ ባለስልጣናቱ በተለያዩ ሚዲያዎች ለምን የምርጫዉ ድመጽ 99.6% እንደሆነ ምክንያት ሲደረድሩ ላየ ሰዉ በርግጥም ሳይተኩሱ መማረክ ይህ ነዉ ያሰኛል!

ከፊሉ ተቃዋሚ ድሮም በምርጫዉ ተሳትፎን የሚደግፈዉ በሂደቱ ኢሕአዴግን እናጋልጥበታለን፣እያደርም በዙሪያዉ ያሉቱን ወገኖች በመሳብ ብቻዉን እናስቀረዋልን፤እንዲሁም ከሕዝባችን ጋር ለመቀራረብ ተጨማሪ በር እናገኛለን፤ በማለት እነጂ የዚህን መንግስት ይዞታ በደንብ ስለሚያዉቅ፣ አሸንፎ የመንግስት ስልጣን እንረከባለን የሚል ቅዠት ስላለዉ ወይም የፓርላማ ወንበር መያዝ ብቻዉን ግቡ ሆኖ አልነበረም።

በሌላ በኩል በተቃዋሚዉ ሕብረት ማጣትና የርስ በርስ መናቆር፣በተለይም በቅንጅት የገንብቶ ማፍረስ ክስተት፣ ከፊሉ ሕዝባችን ደስተኛ ባለመሆኑ “የአህያ ባል ከጅብ አያድንም” ካለ ዉሎ አድሯል። ይህንንም በማለት የወሰደዉ እርምጃ በምርጫዉ ዉጤት ላይ በመጠኑም ቢሆን ተጽዕኖ እንደሚኖረዉ ይገመታል።በምርጫዉ ዉጤት ላይ የአጋጣሚ ተጠቃሚዎች እንሁን እንጂ ለተቃዋሚዎች ዉድቀት ኢሕአዴግ ብቻ ተጠያቂ እንደማይሆን ለሁላችንም እስከአሁን ግለጽ ሊሆን ይገባል። ጥፋታችንንም አለስልሰን በማየት የኢትዮጵያን ሕዝብ ፈሪ ብለን የአባዬን ለእምዬ የሰጠንም አለን። በተለይ ወጣቱን በዉጭ ተቀምጠዉ በስተሰሞኑ ‘ፈሪ’ ብለዉ የሚከሱ የዳር አዋጊዎች፤ መክሰስ ካለባቸዉ የተቃዋሚ መሪዎችን እንጂ ሕዝባችንን አልነበረም።መሪ ከፈራ ሕዝብ ለምን አይሰበሰብ?! እራስን መደለሉን ትተን እዉነቱን እንናገር ብንል፤በተለይ የቅርቡን የትግል ይዞታችንን ስነመለከት፣ ከጥቂት በቃላቸዉ ከተገኙ የተቃዋሚ መሪዎች በስተቀር፣ ከእስር ለመፈታት ጥፋታቸዉን ተቀብለዉ የኢሕአዴግን ‘ምሕረት’ ተንበርክከዉ የተቀበሉ፤ለሕዝቡ የገቡትን ቃል አላየንም ብለዉ አገር ጥለዉ የሸሹ፤ኢሕአዴግ ላይ ከማትኮር ይልቅ እርስ በርስ መወነጃጀልን የመረጡ፣ ዙፋን የለሽ አምባገነኖችና የሹም ሽሮች፣ ስም አጥፊዎችና ምሕረት የለሾች የተቃዋሚዉን ካምፕ አመራር ወረዉት ነዉ የሚታየዉ።ለእዉነተኛ ሕብረት ጆሮዋቸዉን የዘጉ እኒሁ መሪዎች ዛሬም ደግመዉ የኢትዮጵያን ሕዝብ አሳዝነዉታል።እንዴት ታዲያ እኒህ ለወጣቱ አርአያ ሊሆኑ ይችላሉ?! ደግነቱ ሁሉም ጨለማ አይደለም። ብርቱካን መዴቅሳና ሌሎችም መስዋእትነትን እየተቀበሉ ያሉ ጥቂቶች ለወጣቱ እዉነተኛ አርአያ ናቸዉና!

“የኢትዮጵያ ሕዝብ ጀግንነትን ድሮ ቀረ” ስንባል፣ በወንድማማች ሕዝቦች መሐል የተካሄዱ ዉግያዎች ላይ ምሳሌ መስጠቱ ቢያሳዝነንም፣ ሕዝባችን በኤርትራ በሗላም ከሶማሊያ በተካሄዱ ዉግያዎች ያሳየዉ ጀግንነትን ልናስታዉሳቸዉ እንወዳለን። ሕዝባችንን ለዉድቀትና ሽንፈት ያበቁት በፊትም መሪዮች እንጂ የፍርሐት አባዜ ይዞት አይደለም። ይሁንና ከላይ እንደጠቀስነዉ መሪዎቻችን ቢሳሳቱም ለሀገርና ለወገን አልሰሩም ለማለት አይደለም። እጅጉን አስቸጋሪ ሁኔታን ተቋቁመዉ ሕዝባችንን በማደራጀት አለሁልህ በማለትና በቀናነት አገረቸዉን ካስከፊ ሁኔታ ለመከላከል የበኩላቸዉን ሞክረዋል።ዉለታቸዉንም የኢትዮጵያ ሕዝብ አይረሳም። ነገር ግን ለመልካም ስራቸዉ እንደምናመሰግናቸዉ ሁሉ ለተሳሳተ አሰራርና አካሄዳቸዉ በገሐድ ልንተቻቸዉ ይገባል።ጥፋታቸዉን በኢትዮጵያ ሕዝብ ‘ፈሪነት’ ወይም ሌላ ምክንያት ከማላከክ ስሕተቶቻቸዉን በግልጽ መቀበል፣ እዉነትንም መናገር ይገባቸዋል እንላለን።

ስለዚህ ኢትዮጵያን ለማዳን ከዚህ በፊት ከታየዉ የተሻለ እዉነተኝነትና ቻይነት፣ ወኔና ግንባር ቀደምነት፤ የግድ ነዉ። የትግል ስልትንም በተመለከተ መፍትሔዉ አሁንም ተስፋ ሳይቆርጡ በፍጹም ቀናነትና ከላይ የጠቀስናቸዉን እሴቶች ያቀፈ እዉነተኛ ሕብረት ለመፍጠር ጥረት ማድረግ ሲሆን፣ ድርጅቶች ሕብረቱ ዉስጥም እንዲሳተፉ የየበኩላችንን ከፍተኛ ተጽእኖ ልናሳድር ይገባል እንላለን።

ከዚህ በሗላ ወዴት?

የተቃዋሚዉ ጎራ የጊዜያችን ቅድሚያ ጥያቄ ምንድነዉ? ምርጫዉ በትክክል ስላልተካሄደ በፍርድ ቤት ሕግ መጣሱንና መጭበርበር መደረጉን አስመልክቶ ክስ ማቅረብ ወይም ለድርድር ጥሪ ማድረግ? ወይስ ምርጫዉ በትክክል አልተካሄደምና ዳግም ምርጫ ይካሄድ ብሎ ለእዉነትና መብትን ለማስከበር መታገል?

የመጀመሪያዉ ጎዳና አንዳንድ ድርጅቶች ትግሉን በተሻለ መንገድ ያራምደዋል ብለዉ ቢያምኑም፣ በኛ በኩል ግን ለኢሕአዴግ አመች ሁኔታን ይፈጥርለታል እንላለን። ቶሎ መረጋጋትንና ‘ሰላምን’ ያመጣለታል። በተቃዋሚዉ ላይ እጅጉን የሚያስገምት ሁኔታ ስለሚፈጥር ደጋፊዉ ሕዝብ ይሸሻል ፤ የዲሞክራሲ ባላባት ነን የሚሉትም የዉጭ መንግስታት ፕላን ‘ለ’ን ለመመልከት አይፈቅዱም - አንደኛዉን ኢሕአዴግ ጋር ተቃቅፈዉ ይተኛሉ።”ዳግም ምርጫ ቢካሄድ ምን አዲስ ሁኔታ ይኖራል? የዴሞክራሲ ተቋማት እንደሆነ ባንዴ አይገነቡም - እነሱን በድርድርና ትግል ለማቋቋም መጣር ይኖርብናል ” የሚሉት ወገኖች ጊዜዉ ይጠር ይርዘም እንጂ በድምጽ ኢሕአዴግን ማሸነፍ ይቻላል ብለዉ ያምናሉ፤በሂደቱ የዴሞክራሲ ተቋማት ይፈጠራሉም ብለዉ ያምናሉ።እንሂም ወገኖች ለምርጫዉ ሂደትና ዉጤት ተመጣጣኝ ክብደት ይሰጣሉ።

ሁለተኛዉን ጎዳና ስንመለከት፣ በተለይ የዚህ ምርጫ ዉጤት ተቃዋሚዉ በሂደቱ ላይ የነበረዉ ትንሽም እምነት ጨርሶ እንዲሟጠጥ አድርጎታል፣ በመንግስት ተፅእኖ ስር ያለዉ ፍርድ ቤት ላይም እምነት ሊኖረዉ አይችልምና ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ “ፍትሕ” ሊያገኝ ከሚጥር፤ የፖለቲካ ጥያቄዉን አጠናክሮ ከሂደቱ ለመጠቀም ለዳግም ምርጫ መሄድን ይመርጣል።ከምርጫዉ ሳይሆን ከሂደቱ ነዉ የምጠቀመዉ ብሎ ለሚያምን ክፍል የዴሞክራሲ ተቋማት በሂደት ሊፈጠሩ ቢችሉ እንኳ ከብዙ ከባድ ትግልና መስዋዕትነት በሗላ ነዉ ብሎ ስለሚያምን ካሁኑ ኢሕአዴግን ማፋጠጥ የግድ ይሆናል። የትግሉ እሳት የማይጠፋዉም በዚህ ጎዳና ከሄድን ብቻ ነዉ። ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግም ሆነ ህዝባችንን ስብሰባ የመጥራት መብቶቻችን ላይ በመረባረብ በሰላማዊ መንገድ መንግስትን ማስጨነቅ የግድ ነዉ።ለዚህም የመሪዎች ግንባር ቀደም ተሳትፎ የሚያጠያይቅ መሆን የለበትም።ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ በጠበቀን የመንፈስ ጥንካሬ ደረጃ መገኘት ያቃተን የተቃዋሚ መሪዮች ሕዝባችንን ልንክስ የምንችለዉ አሁን ነዉ።

በሁለንተናዊ ትግል የተሰማራን ሓይሎች የሰላዊ ትግሉን አጋዥ አድርገን ስለምንመለከተዉ በበኩላችን በከተሞችና በገጠር ቀበሌ ማሕበራት በተዘረጉ የሕዋስ ድሮቻችን ለትግሉ ድጋፋችንን እንሰጣለን።

ጥር 24 2002 “የአንድነት መዘግየት ለኢሕአዴግ/ሕወሐት የበቀል ሰይፍ ተናጠል ሰለባነት መመቻቸት ነዉ” በሚል አርዕስት ባወጣነዉ መግለጫ የተቃዋሚ ሓይሎች ሕብረት እጅግ አሰፈላጊነትና አጣዳፊነትን ሐትተን እነደነበር ይታወሳል። እዚያም ዉስጥ የ ሚከተለዉን ማለታችንን እናስታዉሳለን፦“...ተቃዋሚዎቹም ለጠነከረ ሕብረት አለመታገላቸዉ ከኢሕአዴግ ያላነሰና ከሕዝብ ፍላጎት የተነጠለ እንቅስቃሴ እያካሄድን መሆናችንን ስንቶቻችን በትክክል እንገነዘብ ይሆን?”

“ትግላችን ከሕዝብ ፍላጎት እንዳይነጠል ከፈለግን የሕብረት ወይም የአንድነት ጥያቄ መመለስ የግድ ነዉ። ...ሓይላችንን አለማስተባበር መጀመሪያ እራሳችንን ማሸነፍ ያቃተን መሆኑን ነዉ የሚያስገነዝበዉ።” እራሱን ያላሸነፈ ወይም ያላረመ ደግሞ የሕዝብን የበላይነት በምንም መልኩ ለማረጋገጥ አይችልም። ስለዚህ የኢሕአዴግ በደል እንዳለ ሆኖ፣ ለሚወክለዉ ሕዝብ ተቃዋሚዉ አሁንም ከተጠያቂነት አይድንም!

ለትግል አንድነታችንና ለምርጫዉ ዳግም መካሄድ ድጋፋችንን እየገለጽን ለዲሞክራሲና ለእኩልነት የሚካሄደዉን ትግል እናጠናክር እንላለን።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

እዉነቱ ያሸንፋል!