የአንድነት መዘግየት ለኢሕአዴግ/ሕወሐት የበቀል ሰይፍ ተናጠል ሰለባነት መመቻቸት ነዉ


ጥር 24 2002

ሰፊዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በአገራችን ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ስርዓት እንዲሰፍን እልህ አስጨራሽ ትግል ሲያደርግ ቆይቷል። ብዙ ስርዓቶችንም ለመቀያየር ምክንያት ሆኗል - በዘለቄታዉ ተጠቃሚ ሌሎች ይሁኑ እንጂ! ያለ ሕግ የሚገሉ አይቷል፤ እራሳቸዉ ያወጡትንም ሕግ ወደጎን ትተዉ እንዳሻቸዉ የሚበይኑትንም እያየ ነዉ።

ስለሆነም ዛሬ ዜጎች አንድም የጭቆናዉን ቀንበር ተሸክመዉ መኖር አልያም ቀንበሩን ከትከሻቸዉ ላይ ለማሽቀንጠር ሲሉ ለማመፅ በሚገደዱበት ሁኔታ ዉስጥ የሚገኙበት ወቅት ነዉ። የመለስ አምባገነን አገዛዝ ከክርናችን በታች ለመኖር የፈለገ ይኑር አልያም ይሰደድ ይህንን አማራጭ ያልተቀበለ ደግሞ የሞት ፍርድ ወይም የእድሜ ልክ እስራት ይገባዋል የሚለዉን መርሕዉን በፍርድ ቤት ደረጃ በቀላጤ በሚታዘዙ አድርባይ ዳኞች ማስፈጸሙን ቀጥሏል።የሰሞኑ ሰለባዎች ደግሞ የግንቦት 7 የፍትህ፤የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አመራር አባላትና ሌሎችም ናቸዉ።በነዚሁ ዳኞች የተላለፈዉ ብይን ለመለስ ተቃዋሚዎች የፖለቲካ “ወየሁላችሁ” መልእክት ነዉ። ታጠቅ ለነጻይቱ ኢትዮጵያ የመለስ የመጨቆኛ መሳሪያ አካል የሆነዉን የ’ፍትሕ ስርዓት’ንና በግንቦት 7 የፍትህ፤የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አመራር አባላትና ሌሎች ላይ በቅርቡ የተላለፈዉን ብይን በጥብቅ ያወግዛል ። ቀኑ የጨለመበት ሕወሓት/ኢሕአዴግ እንደሚያስበዉ ሳይሆን ለማስፈራራት የሚወስዳቸዉ እርምጃዎች የበለጠ ሕዝቡ በሰላማዊ ትግሉ ተስፋዉ እየሟጠጠ ወደ ሁለገብ ትግሉ የሚቀላቀለዉን የሰዉ ቁጥር እጅጉን እየጨመረ እንድሄድ በማድረግ ላይ ነዉ።

ታጠቅ ለነጻይቱ ኢትዮጵያ ለመላዉ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሓይሎች ማሳሰብ የሚፈልገዉ ይህንን አድሏዊና ከፋፋይ አገዛዝ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ትከሻ ላይ ለማስወገድና ከእንደዚህ አይነቱ የቀቢጸ ተስፋ እርምጃ ሕዝባችንን እና አገራችንን ለማዳን ከፈለግን፤ ከምንጊዜዉም በበለጠ በመሰባሰብና በአንድ የጋራ ስምምነት ስር መታገል ይኖርብናል፤ ይህም ጊዜዉ ያለፈበት ወይም ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።

ለሕዝብ ተጠያቂነት የሌለዉ፤ ግልጽነትን የማያዉቅ፤ የመኖሩ ዋና ምክንያት መኖር ብቻ ከሆነ መስተዳድር ምን ይጠበቃል! ነገ በሁለገብ እርምጃ ሊያጠቁኝ ይችላሉ ብሎ ለሚገምተዉ በሙሉ እንዲህ ሸፍጥና ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ መዉሰዱ የሚያስገርም አይደለም። የሚያስገርመዉ ነገም ኢሕአዴግ ሌላ መዓት ይዞ እንደሚመጣ የሚያዉቀዉ በተለይ በዉጭ የሚኖረዉ የተቃዋሚ ሓይል ሕዝቡን መልሶ አለማሰባሰቡ እንጂ!

ታዲያ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ከሕዝብ ፍላጎት እንደተለየ የሚያሳይ ይህን የመሰለ እርምጃ ሲወስድ ተቃዋሚዎቹም ለጠነከረ ሕብረት አለመታገላቸዉ ከኢሕአዴግ ያላነሰና ከሕዝብ ፍላጎት የተነጠለ እንቅስቃሴ እያካሄድን መሆናችንን ስንቶቻችን በትክክል እንገነዘብ ይሆን?

ጠቋሚ ጣትን ሲቀስሩ የአዉራ ጣት ወደማን ይሆን የምታመላክት?! ሕዘባችን “ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ” ካለ ዉሎ አድሯል። በቅንጅትም ጊዜ ተስፋችን ብልጭ ብሎ ጠፋ።በተለይ በዉጭ የሚገኘዉ ከፍተኛ የገንዘብና የእዉቀት ክምችት ያለዉ ኢትዮጵያዊ ለአገሩ ተዓምር መስራት ሲችል፤ ኢሕአዴግ የሕዝብን ፍላጎት በመቃረን የሚፈጽመዉን ያህል ጥፋት እሱ ደግሞ የሕዝብን ፍላጎት ባለመፈጸም ተጠያቂ ሆኗል።

በርግጥ ለሕብረት የሚደረግ ትግል አልጋ ባልጋ አይሆንም። በግል ኤጎ ወይም ከሌላዉ ወገን ጋር ባለመዋደድ፤መሰረታዊ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ ባለመስማማት፤ወይም በፖለቲካም ይሁን በትዉልድ ካንድ አካባቢ ባለመሆናችን ፤ ወዘተ.ሕብረትን ልናንኳስስ ወይም ልናደናቅፍ ፈጽሞ አይገባም።በሕብረት አንድ ላይ መቆም ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሞት የሽረት ጉዳይ ነዉና አንድ ጊዜ ካልሰራ ሁለቴ፤ ሁለቴ ካልሰራ ሶስቴ እየተባለ የማያቋርጥ ጥረት መደረግ ያለበት ጉዳይ ነዉ። ትግላችን ከሕዝብ ፍላጎት እንዳይነጠል ከፈለግን የሕብረት ወይም የአንድነት ጥያቄ መመለስ የግድ ነዉ። ኢሕአዴግ/ሕወሐትን የመሰለ የአገሪቱን ሪሶርስስ ፈጽሞ የተቆጣጠረ ተንኮለኛና ከፋፋይ ሓይል ከፊታችን ተደንቅሮ እንዳንጠቀምበት የሚፈልገዉን የሰዉ፤የገንዘብና የእዉቀት ሓይላችንን አለማስተባበር መጀመሪያ እራሳችንን ማሸነፍ ያቃተን መሆኑን ነዉ የሚያስገነዝበዉ።

ታዲያ እንዴት ከዚህ እንዉጣ? እንዴት ሕብረቱን/አንድነቱን እናምጣ? ለዚሕ ጥያቄ

አንድ ወጥ መልስ ያለዉ አይመስለንም። ነገር ግን ‘ኑ ተሰብስበን ሕብረት እንመስርት’ ወይም በተዘጋጀ የ’ሕብረት ዶክመንት’ ኑና ፈርሙ አይነት አሰራር ከተመክሮአችን ብዙም የተዋጣለት ሆኖ ባለመገኘቱ፤ በምትኩ ለመተዋወቅ፣ ልምዳችንን ለመለዋወጥ፤ የጊዜያችን ሁኔታ የሚጠይቀዉን ሰፊ ሕብረት ለመመስረት ምን ይጠይቅብናል ብሎ ለመጠየቅ የሚያስችል፤ፈረንጆቹ brainstorming ብለዉ የሚጠሩት አይነት ሃሳብ መለዋወጫ ስብሰባ ቢጠራ ተስፋ ሰጭ የመጀመሪያ እርምጃ ነዉ ብለን እናምናልን።

ይህ ስበሰባ ሊፈጥር ይችላል ብለን የምናምነዉ አዎንታዊ መንፈስ ለአዲስ መሰባሰብ ጉልበት ይፈጥራል። ዉጤቱ እንደግምታችን ወይም እንደፍላጎታች ባይሆን እንኳ ከሕዝብ ፍላጎት ላለመነጠል ባደረግነዉ ጥረት ምን እናጣለን?!

በአገር ቤት የመንግስት ተቃዋሚዎች ‘መድረክ’ን መፍጠር እነደቻሉት ሁሉ ጽ/ቤታቸዉን ከአገር ዉጭ ያደረጉ፣ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መስፈን እና ሉዓላዊ አንድነቷ መከበር የሚያምኑ ተቃዋሚ ድርጅቶች በሙሉ የሚሰባሰቡበት መድረክ መፍጠር የግድ ነዉ እንላለን።ያለበለዚይ የሕዝብን ፍላጎት ከመጣስ ባሻገር እራሳችንን የተናጠል ሰለባ አድርገን፤ እንደተለመደዉ ለምእራቡ ዓለም የመለሰ መንግስት እድሜ መራዘሚያ በቂ ምክንያት መሆናችንን እነቀጥላለን።

ከዚህ አንጻር ታጠቅ ለነጻይቱ ኢትዮጵያ፣ ጽ/ቤታቸዉን ከአገር ዉጭ ያደረጉ፣ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መስፈን እና ሉዓላዊ አንድነቷ መከበር የሚያምኑ ተቃዋሚ ድርጅቶች በሙሉ የሚሰባሰቡበት መድረክ ለመፍጠር የመንደርደሪያ ስበሰባ እነዲጠራ ጥሪዉን ያቀርባል።

በዚህ የምትስማሙ ድርጅቶች በሙሉ ድረ ገጻችን (www.tatekethiopia.com) ላይ በሚገኘዉ ኢ-ሜላችን (tatekethiopia@hotmail.com) አማካኝነት ብትገልጹልን ከሁላችንም የተዉጣጣ የስብሰባ አደራጅ ኮሚቴ የሚቋቋምበትን መንገድ አብረን እንፈልጋለን። የዚህ ጥሪ ምላሸ ምን መልክ እንዳለዉም ለሕዝብ ይፋ እናደርጋለን። ከወዲሁ ግለጽ ማድረግ የምንፈልገዉ ሌሎች ድርጅቶች ተመሳሳይ ጥረት በአሁኑ ሰዓት አድርገዉ ከሆነ ወይም በማድረግ ላይ ካሉ ከወዲሁ የኛን የመሳተፍ ፈቃደኝነት ነዉ።

በማጠቃለያ ከዚህ በፊት ለድርጅቶች ሕብረት ወይም ትብብር ከፍተኛ ጥረት ላደረጉ ድርጅቶችና ግላሰቦች ምስጋናና አክብሮታችንን እየገለጽን ከጥንካሬያቸዉም ሆነ ከድክመቶቻቸዉ የምንማርበትን ሁኔታ በመፍጠር የሕዝባችንን ጥሪ ዳግም በመስማት አብሮ ለመስራት ፈቃደኝነታችንን እናሳይ!

የሕወሓት/ኢሕአዴግ ፍትሕ የለሽ ስርዓት በሕብረታችን ይናዳል!

ኢትዮጵያ ለዘልዓለም ትኑር!

ታጠቅ ለነጻይቱ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ

______________________________________________________________________

E-mail: tatekethiopia@hotmail.com www.tatekethiopia.com