ኢትዮጵያ በሕዝቧ አንድነት እንደ ሃገር ትቀጥላለች!


2 ህዳር 2010

11 November 2017

ኢትዮጵያ በሕዝቧ አንድነት እንደ ሃገር ትቀጥላለች!

ታጠቅ በሃገራችን ላይ እየተከሰተ ያለዉን ተለዋዋጭ፣ ፈጣንና አይቀሬዉን የስርዓት ለዉጥ በአጽንኦት ከመከታተልም በላይ የራሱን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል። በሰሞነኞቹ ደግሞ ብሔረሰብን ከብሔረሰብ የማጋጨት ክስተቶች ሰቅዞ በያዘዉ ጭንቀት ዙሪያ እዉነቱን በማፈላለግና መጫወት በሚገባዉ ሚና ዙሪያ ተጠምዶ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ሃገራችን ከስልጣንና ከግዛት ጋር በተያያዘ በጣም ለረጅም ዘመናት በጦርነት አዙሪት ዉስጥ ገብታ ስትባዝን መኖርዋ የአደባባይ እዉነታ ነዉ። ይህንን ከግዛትና ስልጣን ጋር በተያያዘ የጦርነት ታሪክ እጅግ በጣም ብዙዎቹ የዓለማችን አገራት በዉስጡ ከማለፋቸዉም በላይ መቋጫ አግኝተዉለት እና ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነ የስልጣን ሽግግር በማድረግ በስልጣኔ፣ በብልጽግናና በሰላም መኖር ከጀመሩ ዘመናትን አስቆጥረዋል። ኢትዮጵያዊያንና ሌሎች ጥቂት እኛን መሰሎች ግን ዛሬም ድረስ ከሌሎች ተመክሮ እንኳን መማር አልቻልንም። በጣም እጅግ አስፈሪዉ ደግሞ አሁን በስልጣን ላይ ያለዉ ገዥ ፓርቲ መማር አለመቻልም ብቻ ሳይሆን፣ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርና መደላደል ለመፍጠር ጭራሽ ፍላጎት የሌለዉ መሆኑ ነዉ። ይብሱንም ሰሞኑን እያየነዉ ያለነዉ እዉነታ በስልጣን ለመቆየት ስርዓቱ ምንም ከማድረግ የማይመለስ መሆኑን ነዉ።

ኢትዮጵያዊያን በታሪካችን በዙ ጦርነት ዉስጥ መቆየታችን እዉነት የመሆኑን ያህል፣ ብሔረሰብ ለይተን እርስ በእርስ የመዋጋት ታሪክም ሆነ አንዳችን ለሌላችን በሕዝብ ደረጃ ጥላቻ ኖሮንም አያውቅም። በጋብቻ በንግድ እና በሌሎች ማበራዊ መስተጋብሮች መተሳሰሪያችን የላቀዉ የታሪካችን እዉነታ ነዉ። ታዲያ ሰሞኑን በኢሉባቦር የሆነዉን በደራና በገብረ ጉረቻ ሲሆኑ የነበሩት ባእድ ክስተቶች ስንመለከት ግር ተሰኝተን ነበር። ሕዝባችን የተመሰገነ ይሁንና እዉነታዉን ብዙ ሳንዉል ሳናድር እንድናዉቅ አስችሎናል።

ከነዚህ ክስተቶች ጋር በተያያዘ ታጠቅ በተጨማሪ መረጃዎችን እያፈላለገ ቢሆንም እስካሁን ባለዉ መረጃና በደረሰበት ግምጋሜ ይህን ብሔረሰብን መሰረት ያደረገ ግጭት እየፈጠረና እያራገበ ያለዉ የህወሓት/ኢሕአዴግ መራሹ መንግስት መሆኑን በፅኑ ያምናል። ይህ ድርጊት በፈጣሪም ሆነ በህዝባችን ብሎም በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ፊት የሚያስወግዝ ብቻ ሳይሆን ወደር የማይገኝለት የዓለማችን የመጨረሻ ደረጃ ወንጀልም ነዉ። በሕዝብ ፈቃድ ወደ ስልጣን ይመጣል እንጂ፣ ሕዝብን ጨርሶ ወይ አስጨርሶ ስልጣን ላይ አይቆይም። በመሆኑም ታጠቅ የህወሓት/ኢሕአዴግ ሥርዓት ከዚህ የጭካኔዎች ሁሉ ቁንጮ ከሆነ ሰይጣናዊ ተልእኮዉ እንዲቆጠብ በጥብቅ ያሳስባል። እስከመጨረሻዉ ጥፋተኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ በሚያስችሉ ማናቸዉም ሁኔታዎች ላይ ተግቶ ይሰራል። እንዲህ ዓይነት የክፋት ተልዕኮዎች ስኬት እንዳያገኙ አጥብቆ በመስራትም ላይ ይገኛል።

ኩሩዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ሰሞኑን በኢሉባቦር፣ በደራና በገብረ ጉረቻ ላይ ያሳየኅዉ ወገናዊ ፍቅር፣ አብሮ የመኖርና የመከባበር እሴቶች እሰየዉ የሚያሰኙ ናቸዉ። ይህ የአብሮነትና የህዝባችን ፈርሃ እግዚአብሄር ስነልቦና ነዉ ዛሬም ድረስ ለዘመናት ኢትዮጵያን እንደሃገር ጠብቆ ያቆያት። ይህ ኢትዮጵያ ጠላቶቿ እንደሚመኙላት ሳይሆን እንደሃይማኖተኛ ሕዝቧ፣ እንደ ሃገር የምትቀጥል መሆኗን ያረጋገጠ ክስተት መሆኑን ታጠቅ በደማቁ አስምሮበት ማለፍ ይወዳል።

እኛ ስንፋቀር ጠላቶቿ፣ጨቋኞችና አምባገነኖች ዓለም ይጠብባቸዋል፣ይሸማቀቃሉ!ብሎም እንደሃገር የመቀጠላችን እዉነታ የተረጋገጠ መሆን ብቻ ሳይሆን ሌሎቹ ያደረጉትን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርና ዲሞክራሲያዊነት

እዉን አድርገን በሚኖረን ነፃነትና ተነሳሽነት እንበለጽጋለን።

ኢትዮጵያን በሕዝቧ ፍቅር እንደ ሃገር ቀጣይነቷ ያረጋገጣል!