የታጠቅ ኢትዮጵያ ተወካይ በለንደን በ24-25 ፌብሩአሪ 2018 በተካሄደዉ ሁሉን አቀፍ ጉባዔ ያደረገዉ ንግግር Tatek Ethiopia representative's speech at the All-Inclusive Conference held in London on 24-25 February 2018

March 12, 2018

የታጠቅ ኢትዮጵያ ተወካይ በለንደን በ24-25 ፌብሩአሪ 2018 በተካሄደዉ ሁሉን አቀፍ ጉባዔ ያደረገዉ ንግግር

 

Tatek Ethiopia representative's speech at the All-Inclusive Conference held in London on 24-25 February 2018


 

Dear Chairman

Dear PAFD members  

Dear Guests

I will be addressing this meeting in Amharic, but will summarize what I have said in English so that nobody is left out.

Thank you.

 

የተከበሩ የኮንፈረንሱ ሊቀመንበር

ዉድ የ PAFD አባላት

የተከበራችሁ እንግዶች

 

በመጀመርያ በአገራችን ኢትዮጵያ የጨለማዉ ዘመን እያለፈ ውጋገን መታየት የጀመረበት እዚህ ጊዜ ላይ ላደረሰን አምላክ፣ እግዚአብሔር፣አላህ፣ዋቆ ምስጋና ይድረሰዉ እላለሁ።

ባሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በመከሰት ላይ ያለዉን የለዉጥ ሂደት፣ ድርጅቴ በምን መንገድ እንደሚመለከተዉና  ሁላችንም የዜግነታችን መብቶች ተከብረዉ፣ በእኩልነትና በአንድነት በዴሞክራሲያዊ ስርአትና በኢትዮጵያዊነት እሴቶች የምትደዳደር ሃገር እንዲኖረን፣ ምን መደረግ አለበት በሚለዉ የዉይይት አርእስት ለመናገር፣ ዛሬ እፊታችሁ ስቀርብ በታለቅ ደስታ ነዉ።   

 

መግቢያ

ድርጅታችን ፣ ማለትም ታጠቅ ለነጻይቱ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድንት ንቅናቄ (ታጠቅ ለነጻነት) በግንባር መልክ በህቡእ ከተደራጀ ከአሰርት አመት በላይ አስቆጥሯል። ከኢህአዴግ አምባገነን ድርጅትም ጋር ባደረገዉ ተጋድሎ አባላቶቻችን በሜዳ ተሰዉተዋል፣ ታስረዋል፣ተገርፈዋል፣በእስር ማቀዋል። ከአላማችን ግን ዝንፍ ባለማለታችን ይህዉ ለዚህ ቀን በቅተናል።

የድርጅታችን አላማም በአጭሩ:_

 • በኢትዮጵያ የአንድ ድርጅት ፍጹም አምባገነናዊና ዘረኛ ስርአት ተወግዶ፣ በምትኩ በኢትዮጵያዊነት እሴቶች ላይ የተመሰረተች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት ሲሆን፣ ይህም በህዝባችን መሃል እኩልነት፣የህግ የበላይነትና ፍትህ፣ በምጣኔ ሃብት እኩል የመሳተፍ እድል፣ የአንድ ድምጽ ለአንድ ሰዉ የመምረጥና የመመረጥ መብትን፣ የብዙሃን(መድበለ) ፓርቲዎች ስርአትንና የግልና የማህበራዊ መብቶች መከበርን የሚያካት ይሆናል።   

የዛሬ ስብስብ ለዘላቂ መፍትሄ፣ ማለትም አገራችን በአንድነትና በቀጣይነት የሁላችንም የእኩል አገር የመሆን እድል ስለተከፈተላት እንዳለፉት ጊዜያት፣ እንደ 1966ቱና 1983ቱ ዓም የለዉጥ ዘመናት እድላችንን እንዳናባክን አጥብቀን እናሳስባለን።

 

ዛሬ እዚህ ስብሰባ ላይ የመጣነዉ ከናንተ ወንድሞቻችን ጋር፣ እዉነት ላይ የተመሰረተ መተማመን ላይ እንደርሳለን ብለን  በማመን ነዉ። ግልጽነትና እዉነትን ደፍረን የምንጨብጥበት፣ አዲስ ዛመን እየመጣ ነዉና፣ ሌላዉን ሰዉ ለማዳመጥ፣ ሲያስፈልግም እራሳችንን ለመለወጥ ሁላችንም ዝግጁ መሆን እንዳለብን ለማሳሰብ እወዳለሁ።

 

ቀዉስ በኢትዮጵያ?  ቀዉስ በኢትዮጵያ 40 አመት አልፎታል። ባይሆን ዛሬ ያለዉ ቀዉስ ጠቅላይ ቀዉስ ነዉ።

 

የዛሬ ጠቅላይ ቀዉስ ምንጩ ምንድን ነዉ?ምንጩ ብዙ ነዉ፣ ነገር ግን ዋነኛዉ ምንጭ የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት እዉነተኛ ፌዴራላዊ ስርአት (genuine federalism) ለማራመድ ፈቃደኛ አለመሆኑ ነዉ። የህዝብን መብቶች ሸራርፎ በራሱ ማእከልነት የሚመራና እራሱን ብቻ የሚያገለግል ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ መንግስታዊ ስርዓት መፍጠሩና ስልጣንን ሙጥኝ ማለቱ ነዉ።   

የጠቅላይ ቀዉሱ ሁኔታስ ዛሬ ምን ይመስላል? ምን እየሆነ ነዉ?

 

የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት በቀጣይነት ኢትዮጵያን ማስተዳደር ከተሳነዉ ጥቂት አመታትን አስቆጥሯል። በተለይ 3 አመት ወዲህ በኦሮሞ ህዝብ ተጋድሎ፣ በተለይም በቄሮ የኦሮሞ ወጣቶች አኩሪ ተጋድሎ፣ቀጥሎም በጎንደር በተቀሰቀሰዉ እሳት ጎጃምንና ወሎን ጨምሮ ክፉኛ ስርአቱን እየለበለበዉና እያናጋዉ ይገኛል። የህወሃት/ኢህአዴግ ስርአት በሰፊዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ፍጹም ተአማኒነት ማጣት ክፉኛ ጎድቶታል፣ ፖለቲካዊም ይሁን ምጣኔ ሃብታዊ ቀዉስንም አስከትሎ መጥቷል። የዉጭ ምንዛሪ ጠፍቷል፣ የዉጭ መዋእለ ነዋይ ቀንሷል፣ የዉጭ መንግስታት ድጋፍ መመንመን ብቻ ሳይሆን መንግስታቱም ሊከዱት አኮብክባዋል።

ለዚህ የኢህአዴግ መንግስት ምላሽ ግድያና ህዝብን ማሰቃየት በመሆኑ ሃገሪቱ በአመጽ እንድትናወጥ አድርጓል።  አገሪቷ እንደሃገር የመቀጠል እድሏን ጥያቌ ዉስጥ አስገብቷል።ኢህአዴግ፣

 1. በጥልቀት ተሃድሶ አድርጌአለሁ፣ እራሴን አርሜአለሁ፣ ይቅርታም ጠይቄአለሁ በማለት ሊያረጋጋ  ሞክሯል፣ ይህ ጊዜ ለመግዛት ነዉ ወይንስ ከልቡ ነዉ? ጊዜ ይመሰክራል። የኢሕአዴግን መታረም የሚጠላ የለም፣ ነገር ግን እዉነተኝነቱን የምናዉቀዉ ለህዝብ ስልጣን ለመልቀቅ ሲዘጋጅ ብቻ ነዉ። ተግባር ከቃላት የበለጠ ይደመጣልና! ለማንኛዉም በተቃዉሞ ትግሉ መቀጠልና በሱ ላይ ተጽእኖ ማሳደር የግድ ነዉ።   

 2. እስረኛን በገፍ መፍታቱ ለሁለተኛ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ጋር አይጣጣምም

 3. በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መሃል የሚካሄደዉ ትግል እዉነተኛ ይሁን ወይም በዘመናችን ድንቅ የሚያሰኝ የማስመሰል (deception) ጫወታ?   ጊዜ ይነግረናል። የነሱ የ“ለዉጥ” ትርጉም አዲስ ጠ/ሚኒስትር መተካት ብቻ ከሆነ የተቃዉሞ ትግሉ መጠናከር ተመራጮቹን ሊያበረታታ፣ሊያስገድድም ይችላል።

ስለዚህ ለህወሃት/ኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ ምላሻችን፣ ፋታ መስጠት ሳይሆን ይበልጥ ትግሉን ማጠናከር ነዉ!

 

የትግራይ ህዝብን በተመለከተ

በህዝባችን ዘንድ ድሮዉም መሰረታዊ ጠብ አልነበረምና፣ አቶ ለማ መገርሳም በትክክል እንዳስቀመጡት አንዱ ህዝብ የበላይ፣ አንዱ የበታች ሆኖ በታሪካችን አያዉቅምና፣የዚህ አይነት አመለካከት የሚናፈሰዉ ህዝብን ከፋፍለዉ ለመግዛትና እድሜአቸዉን በዚህ ለማርዘም በተነሱ ገዥዎች ነዉ።

ባንድ ወቅት በደልን ጠልቶ ለመብት ትግል የትግራይ ህዝብ በህወሃት ስር ተሰለፎ ነበር። የስልጣኑ ተጠቃሚዎች ግን ጥቂቶች ናቸዉ። እንዲያዩም በትግራይ ህብረተሰብ ላይ ህወሃት ሲመሰረት ጀምሮ ባደረሰዉ ልክ የሌለዉ በደልና አሁን በኢትዮጵያ ላይ ባደረሰዉ ቀዉስ፣ የትግራይ ህዝብ ተባባሪ አይደለም፣ በታሪክ አጣብቂኝ ዉስጥ ስለከተቱትም ፈጽሞ ደስተኛ አይደለም። አንድ ተረት አለ። ላሟ እሳት ወልዳ፣ እንዳትልሰዉ ሊያቃጥላት ሆነ፣ እንዳትተወዉ ደግሞ ልጇ ሆነባት ይባላል። የትግራይ ህዝብ እራሱን የሚገልጽበት አጋጣሚና ሁኔታን እየጠበቀ ያለ ህዝብ ነዉ።  የትግራይ ህዝብን አብረንህ ነን ማለት እንጂ፣ የህወሃት ደጋፊ አድርጎ ማቅረብ፣ አንድም እዉነት አይደለምና እንሳሳታለን፣ ሁለትም የትግራይ ህዝብ ከተቀረዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አለመተባበር የአገራችንን በአገርነት መቀጠል አደጋ ዉስጥ እንደሚከት ማስተዋል ያስፈልጋል። በሶስተኛ ደረጃ የትግራይ ህዝብ ከተቀረዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በተቃዉሞዉ መተባበር የትግሉን ዘመን ያሳጥረዋል፣ ሃዘንና መከራችንንም ይቀንሳል።  

ህወሃት/ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያካሄደዉ የለዉጥ ሂደት በምን መንገድ ነዉ ምላሻ የምንሰጠዉ?

 

መንገዱ አንድ ብቻ ነዉ። የተቃዋሚ ሃይሎች አንድነት ነዉ። ፋታ ሳንሰጥ፣ በአንድነት ትግሉን መርተን እግብ ማድረስ ብቻ ነዉ።

 

ህወሃት/ኢህአዴግ ሲንበረከክ ለመደራደር ዝግጁ ይሆናል፣ ጨርሶ ላለመጥፋት ሲል። ያለበለዚያ “ኢትዮጵያ ትፈርሳለች” እያሉ ማስፈራራት ጊዜዉ አልፎበታል፣ ዛሬ ህዝብ ለህዝብ አይን ለአይን ለመተያየት በቅቷልና። የትግራይ ህዝብ በቅርቡ ትግል ዉስጥ ሲቀላቀል ደግሞ እንዲያዉም መከራችን  ያጥራል። ትግሉ ሲጠናቀቅ ብሄራዊ የመግባባት ዉይይት ተካሄዶ ወደ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ምስረታ እንሸጋገራለን።ይህም የሽግግር መንግስት ህወሃት/ኢህአዴግን እንደሁኔታዉ ሊያካት ይችል ይሆናል።

 

ልደግመዉ እፈልጋለሁ፣

 

ለሽግግር መንግስት መመስረት የሚያበቃን  ቁልፍ ጉዳይ፣ የተቃዋሚ ሃይሎች በጋራ ቆሞ መታገል ነዉ። ይህ ምርጫም አይደለም። የአገር አድን ብቸኛ ጥሪ ነዉ!ተቻችለን በጋራ ካልታገልን ለህዝባችን የምናወርሰዉ ተከፋፍለን መኖርን አይደለም፣ ተከፋፍሎ መጠፋፋትን ነዉ። ሲሪያን ወይም የመንን መሆን አንፈልግም።

 

ስለዚህ በየቦታዉ በብሄራዊ ንቅናቄነት፣በህብረትና በትብብር እየተሰባሰቡ ያሉ ድርጅቶች ጋር፣ ይህ የዛሬዉ ስብስብ የግንኙነት ድር (network) አሁኑኑ በመዘርጋት የጋራ መግባባትን መፍጠር ያስፈልጋል። ይህንንም ለማድረግ ብሄራዊ ሁሉን አቀፍ ጉባኤ በአስቸኳይ እንዲጠራ እንጠይቃለን፣ በዚህ ጉባኤ ይህ ከተወሰነ በበኩላችን በማደራጀቱ ለመሳተፍ ፈቃደኞች መሆናችንን እንገልጻለን። 

ሽግግር ገጽታዉ ምን ይመስላል?

 

በመጅመሪያ በጋራ የሚቋቋመዉ የሽግግር መንግስት እራሱ ዴሞክራሲያዊ መሆን ይኖርበታል። በህግ ፊት እኩልነትን፣ የግልና ማህበራዊ መብቶች እንዲሁም፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች መከበርን ፣ የኢትዮጵያዊነት ባህላዊና እምነታዊ እሴቶችን ያቀፈ እንዲሆን ያስፈልጋል። ከዚህም በአሻገር ምርጫ ማካሄድ የመጨረሻዉ ግብ አለመሆኑን ተገንዝቦ ነጻ ሚዲያና በህግ ፊት በእኩልነት መታየትን፣ እንዲሁም ከህግ ዉጭ ያለመታሰርን መብቶች በስራ ለይ እንደሚዉሉና ለነዚም አስፈላጊ ተቋማት መተከላቸዉን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።  

 

አደራ የምንለዉም ጉዳይ፣ አዲስ ዘመን አዲስ አመለካከትን ይጠይቃል። የወደፊቱ አዲስ ስርአተ-መንግስትም በአዲስ አመለካከት ላይ የተመሰረተና ዘላቂነት ያለዉ መሆን ይኖርበታል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ከራሳችን ዉጭ ባሉና የተለዩ አመለካከቶችን ለማስተናገድ ፍጹም ፈቃደኛ መሆን ያስፈልጋል፣ በድሮ አመለካከት አዲስ ስርአት እንደማይገነባ መቀበል ይኖርብናል።

 

በስተቀረ የሽግግር መንግስት ምስረታና ቁልፍ ተግባራት ወይም ዋነኛ ግቦች ምን መሆን አለባቸዉ ለሚለዉ ተግባራትንና ግቦችን መዘርዘር ከጊዜ አንጻር አስፈላጊ ባለመሆናቸዉ ወደ መደምደሚያ እንድሄድ ይፈቀድልኝ።

 

 መደምደሚያ:

ዛሬ በኢትዮጵያ የጠቅላይ ቀዉሱ ዋንኛ ምክንያት ህወሃት ነዉ፣ ለለዉጡም ዋንኛ እንቅፋት እሱዉ ነዉ። ዛሬ የኢትዮጵያን ህዝብ መናበብ ስንመለከት፣በተለይ ኦሮሞዉ፣አማራዉ፣ ጉራጌና ሌሎችም ህብረተሰቦች ትግላቸዉን ለማቀናበር ጥረት ሲያደርጉ፣ በኢትዮጵያ ባለድርሻነት፣በያገባኛልነት ብዙ የህብረተሰብ የፖለቲካና ማህበራዊ ድርጅቶች ሲታገሉና ለመቀናጀት ጥረት ሲያደርጉ ስናይ፣ ተስፋ የሚሰጥና ሁላችንም ተግባብተን በጋራ ልንኖርባት የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ ቅርብ እንደሆነች መገመት ይቻላል። የትግራይ ህዝብም እኩል ተበዳይና የመፍትሄዉ አካል እንደመሆኑ በቅርቡ ይቀላቀለናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ለኛ ቅድሚያ ጉዳይ የተቃዋሚዎች ህብረትና አድነት ስለሆነ የዛሬዉ ስብሰባ ይህን ለማሳካት ቃል መግባት አለበት። በስተቀረ ቸር ተመኝ፣ ቸር ታገኛለህ ነዉና፣ በቅርቡ ከእስር በተፈታው እውቁ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ንግግር በመጥቀስ ንግግሬን ልቋጭ:- እስክንድር ነጋ ከእስር ቤት ሲፈታ እንዲህ አለ፣

“ከፊት ለፊታችን ብሩህ ዘመን ይጠብቀናል፡፡ ታሪክ ከእኛ ጋር ነው፡፡ እውነት ከእኛ ጋር ነው፡፡ ፍትሕ ከእኛ ጋር ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ ሁሌም ቢሆን የተበዳይ መከታ የሆነው ፈጣሪ ከእኛ ጋር ነው፡፡ የድል አክሊል ይጠብቀናል፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው በትግላችን ጽናት፣ በአካሄዳችን መቻቻል፣ በመንፈሳችን ፍቅር፣ በአስተሳሰባችን ሚዛናዊነትና በተግባራችን ሠላምን ይዘን ወደፊት መጓዝን ነው፡፡”

 

ኢትዮጵያ ለዘልዓለም ትኑር!

አመሰግናለሁ።

 

Summary in English:

 • The core reason for the great crisis Ethiopia finds itself today is the denial of genuine federalism by the government. It has fostered a highly centralised unitary rule, with TPLF at the centre of power, with total curtailment of political space.

 • The solution is now in the hands of the people. The government has had so many chances in the past to make things right, but used them only to further its stay in power. It now appears that it has lost total credibility in the eyes of the Ethiopian people, who are truly disappointed of its deceptions and empty promises.

 • The corrective measures which have been offered by the government such as the recent release of prisoners are welcome. However, this has been contradicted by the Marshall Law. If the government is genuine in its intentions, we want concrete and genuine actions towards opening the political space and participation of the opposition in the fate of the country, as we know action speaks louder than words.

 • In the mean time the most crucial remaining question is what guarantees are given that the changes promised will be delivered? It would appear that the only existing guarantee is the continuation of the peaceful protests!

 • With this in mind, we would like to extend our great respect to those at the forefront of the struggle, the Keerros, the Fannos, the Zerma, and all who have went into the streets and continue to take part in the struggle directly and those who participated indirectly, through the provision of finance and other means including their prayers.     

 • However, as unity of leadership is key in our struggle for democracy and freedom, we call upon all opposition parties both within and outside of the country, to make  stronger commitment to extend their hands towards each other and secure new heights of unity. Forming such a common front would at the minimum, enable the creation of a transitional body which will bring about the necessary changes towards a democratic system of government of unity and freedom.

 • Tatek Ethiopia is happy to work with the PAFD and all others here and away in making our common dream come true!

The struggle continues!

Long live Ethiopia!

Thank you.

Share on Facebook
Share on Twitter
Please reload